ብቁና በፈጠራ ክህሎት የተካነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራሁ ነው- የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ

52

ጎባ መጋቢት13/2011 በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ  ብቁና በፈጠራ ክህሎት የተካነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በሥራ ፈጠራ ጥበብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በስልጠና ለመሙላት ለ600 ወጣቶች የተዘጋጀው የአንድ ሳምንት ስልጠና ተጠናቋል።

የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መሐመድ ሁሴን በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የሰው ኃይል ለማፍራት ጥረት እያደረገ ያለው የዘርፉ ተግዳሮቶችን በጥናትና ምርምር  በመለየት ነው፡፡  

ማዕከሉ ባለፈው ዓመት አንድ ሺህ ለሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው ምሩቃንና ለአካባቢው ወጣቶች ከኦሮሚያ ኢንተርፕርነርሽፕ ማዕከል ጋር በመተባበር ተግባር ተኮር ሰልጠና መስጠቱን አስታውሰዋል።

በቀጣይም የአንቀሳቃሾችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ስልጠና በመስጠት አቅማቸውን የሚገነባበት ስልጠና  እንደሚሰጥ አስተባባሪው አስታውቀዋል።

ከጎሎልቻ ወረዳ የመጣው ወጣት ሐሰን ዑስማን በሰጠው አስተያየት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ ሥራ ቢጀምሩም፤ ከቢዝነስ አስተዳደር ግንዛቤ እጥረት በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ገልጿል፡፡ 

ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸው በተግባር የተደገፈ ስልጠና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን አቅም እንደፈጠረላቸው አስረድቷል።

ከሲናና ወረዳ የመጣችው ወጣት አልማዝ በየነ በበኩሏ ከአንድ ዓመት በፊት ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ብትመረቅም፤የግል ሥራ ለመጀመር ከፍተኛ ካፒታል ያስፈልጋል በሚል ስጋት በቤተሰብ ላይ ጥገኛ ሆና መቆየቷን አስረድታለች።

በአካባቢው ላይ የሚገኙ የተለያዩ አማራጮችን በመፈተሽ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ከስልጠናው መረዳቷን ተናግራለች።

በጥልፍ ሙያ ሥራ ለመጀመር መነሳሳት እንደፈጠረላትም አልማዝ  አስታውቃለች።

የኦሮሚያ ሥራ ፈጠራ ማዕከል ተወካይ አቶ ኃይሉ ሻምበል ማዕከሉ በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የሥራ እድል ፈጠራ ዘርፍን ከሚመሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር በሥራ ፈጠራ ጥበብ፣ በሂሳብ መዝገብ አያያዝ፣በቢዝነስ እቅድ አዘገጃጀትና በሌሎች መስኮች የተሰጠው ስልጠና የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ100 የሚሆኑ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም