አሜሪካ ወደ ሀገሯ በሚገቡ የብረትና የአልሙኒየም ምርቶች ላይ ቀረጥ ጣለች

126
ግንቦት 24/2010 አሜሪካ ከአውሮፓ፣ ሜክሲኮና ካናዳ ወደ ሀገሯ በሚገቡ የብረትና የአልሙኒየም ምርቶች ላይ ቀረጥ ጣለች፡፡ የአውሮፓ ህብረትም አፀፋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። ከቀረጥ ነፃ የሚገቡበት የሁለት ወር እፎይታ ማብቃቱን የገለፀው የትራምፕ አስተዳደር ከዋነኛ የንግድ አጋሮቹ ጋር የንግድ ጦርነት ከፍቷል። የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ዊልበር ሮስ ለጋዜጠኞች በስልክ እነደተናገሩት፥ በብረት ምርቶች ላይ 25 በመቶ እና በአሉሚኒየም ምርቶች ላይ 10 በመቶ ቀረጥ ተጥሏል። ከካናዳና ሜክሲኮ ጋር በሰሜን አሜሪካ ነፃ የንግድ ስምምነት ዙሪያ ለመግባባትና ለመወያየት የተደረገው ሙከራ ያለስኬት ረጅም ጊዜ ወስዷል ነው ያሉት። የአውሮፓ ህብረት ምርቶችን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ እንዲያስገባ በተሻለ መልኩ ድርድር ቢደረግም የቀረጥ እፎይታ ጊዜውን ለማራዘም በቂ ሁኔታ አላገኘንም ነው ያሉት። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዢያን ክላውድ ጀንከር በበኩላቸው ህብረቱ በአሜሪካ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአፀፋ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል። የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት “የዛሬዋ እለት ለዓለም ንግድ መጥፎ ቀን ናት” ማለታቸውንም የአልጀዚራ ዘገባ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም