በሰብአዊ መብት ጥሰት የተከሰሱት እነ ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፈአይኔ ያቀረቡት በዋስ እንለቀቅ ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

91

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተከሰሱት እነዋና ሳጅን እቴነሽ አረፈአይኔ ያቀረቡትን በዋስ እንለቀቅ ጥያቄ ውድቅ አደረገ።

በነኮማንደር አለማየሁ የክስ መዝገብ ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፈአይኔን ጨምሮ 10 ሰዎች በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ ተመስርቶባቸዋል። 

ተከሳሾቹ ዛሬ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 12ተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ነው በዋስ እንለቀቅ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት።

ተከሳሾቹ 'በአቃቢህግ የቀረበው ክስ የዋስትና መብት የሚያስከለክል አይደለም፤ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ሕገ-መንግስታዊ መብታችን በማጤን የዋስትና መብት ይስጠን' ሲሉ በጠበቃቸዉ በኩል ጥያቄውን አቅርበዋል።

አቃቢ ሕግ በበኩሉ "ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ተደራራቢ በመሆኑና ጥፋተኛ ሆነዉ ከተገኙ እስከ 15 እና ከዛ በላይ የሚሆን እስር የሚያስቀጣ በመሆኑ የዋስትና መብት ቢሰጣቸዉ በቀጠሮዋቸዉ ቀን ይቀርባሉ የሚል እምነት የለኝም" ሲል ተከራክሯል።

አቃቤ ህግ አክሎም ተከሳሾቹ በዋስ ቢለቀቁ ምስክሮችን ሊያባብሉና ሊያጠፉ ይችላሉ በማለትም ገልጿል።

የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረዉ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ጥያቄዉን ዉድቅ አድርጓል።

በመጨረሻም ተከሳሾች ባቀረቡት መቃወሚያና የአቃቢ ሕግን ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሚያዚያ 4 ቀን 2011 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም