በደቡብ ክልል በበልግ ወቅት እርሻ ከ129 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ይጠበቃል

68

ሆሳዕና መጋቢት 13/2011 በደቡብ ክልል በበልግ ወቅት ከሚለማው መሬት ከ129 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

በክልሉ የበልግ ሥራዎች ላይ ያተኮረ የአመራር ንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡

አመራሩ የበልግ  ወቅት እርሻን ውጤታማ በማድረግ በመኽርና በመስኖ ልማት ያጋጠመውን ምርት ማካካስ እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡

በቢሮው የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ምርቱ የሚጠበቀው የወቅቱን ዝናብ ጠብቆ ከሚለማው ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ ነው።

ለዚህም 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚቀርብና የሰብል ምርጥ ዘርን ጨምሮ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የድንችና የስኳር ድንች  ዝርያዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የበልግ እርሻ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ስለሚመረትበት ከዝግጅቱ ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ አመራሩ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ኃላፊው አሳስበዋል።

አርሶ አደሮችን በማሰልጠንና ተከታታይነት ያለው ድጋፍ በማድረግ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አመራሩ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከሥራው የተለየውን አርሶ አደር ወደ ልማቱ በመመለስ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

አመራሩ የዘመኑን በልግ  ወቅት እርሻን ውጤታማ በማድረግ በ2010/11መኽርና በመስኖ ልማት ያጋጠመውን ምርት እንዲያካክስ ተጠይቋል፡፡

የወላይታ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ኃላፊ አቶ አሞና ቶልካ እንደገለፁት በዞኑ በበልግ ወቅት 128 ሺህ ሄክታር መሬት የሚለማ ሲሆን፣ 68ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል፣ ቀሪው በስራስርና በፍራፍሬ እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

ለአርሶ አደሮቹ 182 ሺ ኩንታል ማዳበሪያና 57ሺ 800 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ነው ብለዋል፡፡

የከምባታ ጠምባሮ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስራት ማቲዎስ በበኩላቸው በዞኑ 6ሺህ ሄክታር መሬት በበቆሎ እንደሚሸፍን ገልጸዋል።

ለዚህም ከሚያስፈልገው  ከ1ሺህ 600 በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር  ውስጥ  እስካሁን የቀረበው 600 ኩንታል ብቻ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የበልግ ምርት በዋና ዋና ሰብሎች እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ምርት እንደሚያስገኝ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም