የልዑል አለማየሁ አፅም ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ተጠየቀ

113

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 የአጼ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል አለማየሁ አፅም ወደ እናት ሀገሩ እንዲመለስ ተጠየቀ።

በቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድን በለንደን ጉብኝት አድርገዋል።

በዚሁ ወቅትም በለንደን የዊንዶዘር ቤተመንግስት የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስን መካነ መቃብር እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አፄ ሃይለስላሴ ይጸልዩበት የነበረውን ወንበር ጎብኝተዋል።

ዶክተር ሂሩት ካሣው በአጼ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር  የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በጉብኝቱ ወቅትም "የአጼ ቴዎድሮስን ፀጉር ማግኘታችን ደስ ብሎናል፤ ይሁን እንጂ ከትውልድ ቦታው ተለይቶ ህይወቱ ያለፈው ልዑል አለማየሁ አፅም በትውልድ ሀገሩ እንዲያርፍ የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ስለሆነ በክብር ወደ አገሩ እንዲመለስ" ሲሉ ዶክተር ሂሩት ጠይቀዋል።

አዕሙ ወደኢትዮጵያ ተመልሶ ከአባቱ አጼ ቴዎድሮስና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መቀላቀል እንደሚገባውና የዊንዶዘር ቤተመንግስት ለሚመለከተው አካል ጥያቄውን አቅርቦ በአፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።

በዕለቱ ልዑካን ቡድኑን በመቀበል ከቡድኑ ጋር የተወያዩት የዊንዶዘር ቤተ-መንግስት ሃላፊ ዶክተር ማርክ ፓወል በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንነጋገርበታለን ብለዋል።

ሂደቱን በተመለከተ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመከታተል እልባት እንዲያገኝ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግም ሚኒስቴሩ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የልዑካን ቡድኑ ትናንት ለንደን የሚገኘውን የቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ጎብኝቷል።

የባህልና ቱሪም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው የተመራው የልዑካን ቡድኑና በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሙዚየሙ ዳይሬክተር ዶክተር ትሪስትራም ግራንት ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ወቅት በቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄ ቀርቧል።

እ.አ.አ በ2018 የቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም የሚገኙ የመቅደላ ስብስብ ቅርሶች ለኢትዮጵያ መመለስ እንደማይችል፤ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ውሰት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚቻል መገለጹ ይታወቃል።

የሙዚየሙ ዳይሬክተር ሚስተር ትሪስትራም ግራንት ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ውሰት የሚለው ቃልም ለኢትዮጵያውያን ከባድ መሆኑን እንደተረዱት ተናግረዋል።

በመሆኑም "የተቸገሩት ጉዳዩ የህግ ጉዳይ በመሆኑና ምላሽ ለመስጠት ያለን አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው " ብለዋል።

"ያለን አማራጭ ይህን ቀዳዳ በመጠቀም ሊስተካከሉ የሚችሉ አባባሎችን ተጠቅመን የሚመለሱበትን ሁኔታ መፍጠር፤ ይህን ካላደረግን ግን በህጉ ላይ ፀንተን ወደፊት የሚሆነውን ነገር መመልከት ይኖርብናል" ሲሉም አክለዋል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ቅርሶቹ የኢትዮጵያ በመሆናቸው በረጅም ጊዜ ውሰት ሳይሆን በቋሚነት ቅርሶቹ ለኢትዮጵያ መመለስ የሚችሉበት አማራጭ መፍትሄ ሙዚየሙ ሊያበጅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በኤምባሲውና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል በአስቸኳይ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም፤ ካለው ህግ ጋር በማይጋጭና የኢትዮጵያን ጥያቄ ሊመልስ በሚችልበት ሁኔታ በመንቀሳቀስ ጉዳዩ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት እልባት እንደሚያገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸፀዋል። 

በለንደን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ባለው ሙሉ አቅምና ጊዜ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት በመወጣት ቅርሶቹ ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጉ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻወል ገልጸዋል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው የተመራ ልዑካን ቡድን በእንግሊዝ የሚገኙ ቅርሶችን ማስመለስ አላማ ያለው ጉብኝት ለማድረግ መጋቢት 9 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ስፍራው እንዳቀና የሚታወስ ነው።

ከትናንት በስቲያ የብሪታንያ ብሔራዊ ጦር ቤተ-መዘክር የአጼ ቴዎድሮስ ሽሩባ (ቁንዳላ) ለኢትዮጵያ መንግስት ማስረከቡ ይታወቃል።

ልዑካን ቡድኑ በእንግሊዝ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው የተመራው ልዑካን ቡድን ነገ ረፋድ ላይ ከእንግሊዝ የተረከበውን ታሪካዊ ቅርስ ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል።

የኢትዮጵያ ቅርሶች በአብዛኛው በእንግሊዝ፣ በጀርመንና በጣልያን አገር የሚገኙ ሲሆን ወደ አገር ቤት ለማስመለስ በአገሮቹ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም