አየር መንገዱ የአደጋው የምርመራ ውጤት እስኪታወቅ ማንኛውም አካል የተሳሳተ መረጃ ከማውጣት እንዲቆጠብ አሳሰበ

113

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ በምርመራ እስኪጣራ ማንኛውም አካል የተሳሳተ መረጃ ከማውጣት እንዲቆጠብ አሳሰበ።

በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ድረ-ገፅ ላይ ''የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማክስ 8 ምስለ-በረራ (ሲሙሌተር) ነበረው አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን አብራሪ ግን ስልጠናውን አልወሰደም'' በሚል አብራሪው በቂ ስልጠና አለመውሰዱን የሚገልጽ ዘገባ ማቅረቡ የተሳሳተ ከመሆኑ ባለፈ አየር መንገዱን ያሳዘነ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ላይ በበረራ ደህንነታቸው ከሚታወቁ አየር መንገዶች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

ይሁንና መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ሲጓዝ አደጋ ደርሶበት የ35 አገራት 149 መንገደኞችና ስምንት የበረራ አስተናጋጆች ህይወት ማለፉ ይታወቃል።

ከወራት በፊት የኢንዶኔዥያ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከአገሪቱ መዲና ጃካርታ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በመከስከሱ የ189 ሰዎች ህይወት ማለፋቸውም ይታወሳል።

ይህ አደጋ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት ከሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ የዓለም አየር መንገዶች ያሏቸውን ቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ ውጭ አድርገዋል።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ሲሆን የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን በአደጋው መንስኤ ላይ የተለያዩ መላምቶች ማስቀመጣቸውን ቀጥለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የአየር መንገዱ ቦይንግ 737 ማክስ ስምንት አብራሪዎች ቦይንግ ባወጣውና በፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በፀደቀው በቦይንግ 737 ኤን ጂና በቦይንግ 737 ማክስ ያለው ልዩነት ላይ በቂ ስልጠና  ወስደዋል።

ቦይንግ 737 ማክስ ወደ አየር መንገዱ ከመግባቱ አስቀድሞና በረራ ከመጀመሩ በፊትም ለአብራሪዎቹ አስፈላጊው ስልጠና ተሰጥቷል።

የአሜሪካው ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በኢንዶኔዥያው ላየን ኤር የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ባወጣው ተጨማሪ የስልጠና መመሪያ መሰረትም ለሁሉም አብራሪዎች ደረጃውን የጠበቀ ገለጻ መደረጉን አየር መንገዱ አስታውቋል።

የመመሪያው ይዘት በስልጠና ማንዋል፣ በኦፕሬሽን ዝርዝር መመሪያዎችና በዕለት ተዕለት ስራዎች ላይ እንደተካተቱም ነው የተብራራው።

ይሁንና የአደጋው የምርመራ ውጤት ሳይታወቅ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየወጣ ያለው የተሳሳተ ዘገባ ትክክል አለመሆኑንና የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር መገናኛ ብዙሃን የተዛባ መረጃ ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ አየር መንገዱ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም