ከኢሉአባቦር ዞን ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው የቡና ምርት መጠን እያደገ ነው

56

መቱ መጋቢት 13/7/2011 በኢሉአባቦር  የቡና ልማትን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው ምርት መጠን እያደገ መምጣቱን  የዞኑ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት በዞኑ የቡና ልማትን ለማስፋፋት በየዘመኑ ከ100 ሺህ የሚበልጡ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ሲተከሉ ቆይተዋል፡፡

ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኙት ከአካባቢው ጋር በማዳቀል የተዘጋጁት እነዚህ የቡና ዝርያዎች  ከነባሩ በሄክታር  የሚገኘውን ስድስት ኩንታል ምርት በእጥፍ ማሳደግ ተችሏል።

ይህም በዞኑ ተመርቶ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው የጥራቱን የጠበቀ የምርት መጠን እያደገ እንዲመጣ ማስቻሉን የባለሥልጣኑ ስራ አስከያጅ አቶ አዲሱ ንጉሴ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሰባት  ወራት ለዚሁ ገበያ  የቀረበው 12 ሺ 270 ቶን የቡና ምርት ከቀዳሚው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር  በ2 ሺ 400 ቶን  ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል።

አቶ አዲሱ እንዳሉት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች አቅርቦት በተጨማሪ ከችግኝ ተከላ አንስቶ ምርቱን ለገበያ እስኪያቀርቡ  ድረስ ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያደርጉ በባለሙያ  ምክርና እገዛ መደረጉ ለምርት ጥራት መጠበቀም አስተዋጽኦ አድርጓል።

ከዚህ ቀደም እስከ ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃ ሲወጣ የነበረው የአካባቢው ምርት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እስከ ሶስተኛ ደረጃ እያገኘ ነው፡፡

በዞኑ የሚመረተው የቡና ምርት ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር አንስቶ በኢሉባቦር ስም ለማዕከላዊ ገበያ መቅረብ መጀመሩም  በልማቱና ግብይቱ ይበልጥ መነቃቃት ፈጥሯል፡፡

ምርቱ በብዛት ለገበያ የሚቀርበው ከአሁን በኋላ በመሆኑ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ከ32 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ  ገበያ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

በዞኑ የሚገኙ 554 ቡና አቅራቢ ነጋዴዎችና 58 ማህበራት ምርቱን ከአርሶ አደሩ በማሰባሰብ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ያመለከቱት ስራ አስኪያጁ   የምርቱን ጥራትና ብዛት ይበልጥ   ለማሳደግ ከአቅራቢዎችና ከአርሶአደሩ ጋር  በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አለማየሁ ሽፈራው በዞኑ አሌ ወረዳ የገርበዲማ ቀበሌ አርሶ አደር ሲሆኑ ከአስር ሄክታር የሚበልጥ መሬት ከደን ጋር በጥምር  ከሚያለሙት ቡና በየዓመቱ እስከ 60 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆኑን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት ቀይ ቡና ብቻ በመሰብሰብና ጥራት ባለው ማድረቂያ ምርቱን በማዘጋጀታቸው ከልማቱ ተጠቃሚ ናቸው።

በመቱ ወረዳ በቡና ንግድ የተሰማሩት አቶ ግዛው ግርማ በበኩላቸው ጥራቱን የጠበቀ ምርት ብቻ በመሰብሰብ ለገበያ ማቅረብ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ  ተግባራዊ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

" የግብይት ማዕከል በቅርበት ስለተከፈተልን ለምርቱ ጥራትና ብዛት ይበልጥ እንሰራለን"  ያሉት ለዚህም አቶ ግዛው ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ያሉ ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በኢሉአባቦር ዞን ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ ሲሆን ከ200 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ናቸው።

በየዓመቱም ከዞኑ ከሚመረተው 60 ሺህ ቶን ምርት ውስጥ 23 ሺህ ቶን የሚሆነው ለማዕከላዊ ገበያ እንደሚቀርብ  ከዞኑ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ባለስልጣን የተገኛው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም