“ከመቃብር አውጥቼ---?”

52

ደሳለኝ ካሳ /ኢዜአ/በሰው ልጅ ዘንድ  የከበረና  ከፍ ያለ ዋጋ  የሚሰጠው  ወርቅ፣ አልማዝ ወይም ሌሎች ቁሶች አይደሉም፡፡ የሰው ጤናና ህይወት ትልቁን ቦታ ይይዛልና። ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን ለሚያከብሩት ሰው ሰላምታ  ሲያቀርቡ  ወርቅ  ይስጥልኝ፣ አልማዝ  ይስጥልኝ  ሳይሆን  ጤና ይስጥልኝ ብለው እጅ የሚነሱት፡፡

ታዲያ ለጤና የምንሰጠው ዋጋ እንደዚህ  ከፍ ያለ ከሆነ ለጤና ተቋማት የምንሰጠው ትኩረት  ምን ይመስላል? ተደራሽነታቸውስ?

ዛሬ ዛሬ ጊዜ ወለድ በሽታዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፤ የሰውልጅ  የአኗኗር  ዘይቤ፣  የአመጋገብ ስርዓት፣ የምግቡ አይነት፣የአካባቢ አየር ብክለትና መለዋወጥን ተከትሎ  የማይተላለፉ በሽታዎች እንደ ደም ግፊት፣  ስኳርና ካንሰር  በቀዳሚነት  ይጠቀሳሉ፡፡  

ሰሞኑን ወደ ጥቁር አንበሳ  ሆስፒታል ጎራ ብለን ያየናቸውንና የሰማናቸውን ልብ የሚነኩ ታሪኮች ልናካፍላችሁ  ወደናል፡፡

ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በጥቁር አንባሳ  ሆስፒታል ህክምናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የካንሰር ህሙማን ህክምናውን ለማግኘት  በሚያደርጉት ውጣ ውረድ  ያጋጠማቸውን እንግልት በሰማን  ጊዜ ለነገ የማይባል ጉዳይ  ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

አቶ ሙህዲን ከድር ይባላሉ፤ የወሊሶ ነዋሪ  ናቸው ፡፡ አቶ ሙህዲን ባለቤታቸው የማህጸን ጫፍ ካንርሰር ታመውባቸው ለማሳከም ያዩትን ውጣ  ውረድ እንዲህ ይናገራሉ፡፡ የወሊሶ ሆስፒታል የማህጸን ጫፍ ካንሰር መሆኑን በማረጋገጥ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር ይጽፍላቸዋል፡፡ ሪፈሩን ይዘው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያመራሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምናውን ለመጀመር ላይ ፣ታች ሲሉ ቆይተው  ከሁለት ወራት ደጅ መጽናት በኋላ ወደ ካንሰር ክፍል ይላካሉ፡፡

“ወደ ካንሰር ክፍል እንደተላክን ህክምናውን  እንጀምራለን ብለን ተስፋ ስናደርግ  ይባስ ብሎ  ለአንድ አመት ወረፋ መጠበቅ  እንዳለብን ተነገረን” በማለትም ነው  ብሶታቸውን የሚናገሩት።   በቀጠሮው  መራዘም ግራ  የተጋቡት  አቶ ሙህዲን  “የካንሰር በሽታ ቆሞ ይጠብቃል?  ወይስ የዛሬ አመት ከመቃብር  አውጥቼ  ነው የማሳክማት?”  በማለት  ለህክምና ባለሙያዎች  ጥያቄ  አዘል ቅሬታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

ለዚህ ጥያቄያቸው በሆስፒታሉ በሚሰጠው በማታው የግል የክምና አገልግሎት ማሳከም እንደሚችሉና ለህክምና እስከ 20ሺ ብር እንደሚያስፈልግ እንደተጠየቁ ይናገራሉ፡፡ አቶ መህዲን ተቀጥረው ከሚሰሩበት የሳሙና ፋብሪካ የሚያገኙት የ2ሺ ብር ከፍሎ ለማሳከም ባያስችላቸውም ላለመስማማት  አማራጭ የላቸውም፡፡ ዳሩ ግን በሆስፒታሉ የሚሠጠውን የግል ህክምና አገልግሎት ለማግኘትም  ቢሆን ለአራት ወራት መጠበቅ  ይኖርባቸዋል፡፡

የሆስፒታሉ አላማ ህይወትን ማዳን ቢሆንም  ቸልተኝነት  ይስተዋላል፣ አለፍ ሲልም ከገንዘብ ጋር በማያያዝ በግል ወደ ሚሰጥ  ህክምና ይገፉታል በማለት በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የታዘቡትን ይናገራሉ፡፡

የሆስፒታል አገልግሎት እንደ መብራት፣ ውሃ አግልግሎት ሳይሆን ህይወትን የማዳን ጉዳይ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሠጠው ይገባል የሚሉት አቶ ሙህዲን በአግልገልግሎት አሰጣጡ ተስፋ በመቁረጣቸው “ብታመም ሆስፒታል እንዳትወስዱኝ ብዬ  ተናዝዣለሁ ” ነው ያሉት።

ከሚኖሩበት ወሊሶ ከተማ እየተመላለሱ ህክምውን መከታተል ሌላኛው ችግር ከመሆኑም  ባለፈ  ለማሳከም በመጡበት ከስራ ቀርተዋል በሚል የአራት ወራት ደሞዛቸውን ተከልክለዋል፡፡ ደሞዛቸውን ማጣታቸው ጉዳዩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል-የኢኮኖሚ ጫናውን ያበረተዋልና ፡፡

ቦርቆ ያልጨረሰ የ12 አመት ታዳጊው ነው፡፡ በአፍንጫው ዙሪያ ያለው የሰውነት ክፍል ተላልጧል፡፡ በደም ካንሰር ከተያዘ ሶስት አመታትን እንዳስቆጠረም ይናገራል።ታዳጊ አባይነህ ቢረሳው፡፡

አባይነህ ህክምናውን በጥቁር አንባሳ ሆስፒታል በመከታተል ላይ ነው፡፡ በበሽታው ምክንያት  ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዷል፤ ከእኩዮቹ ተነጥሏል፤ ከቤተሰብም ርቋል፡፡ በርግጥ አባቱ ከጎኑ ሆነው  ለማሳከም ላይ ታች  እያሉ ነው፡፡  ታዳጊው ታክሞ ለመዳን ያለው ጉጉት  ከፊቱ ላይ ሲነበብ ልብን ይሰብራል፡፡

ታደጊው ህክምናውን ከጀመረ ወዲህ ከበሽታ ጋር በተያያዘ  በአካሉ ላይ የነበረው እብጠት ቢቀንስም መድሀኒቱ በሚጠፋበት ጊዜ ህክምናው ስለሚቆራረጥ በጤናው ላይ ችግር እየገጠመው መሆኑን ይናገራል፡፡

የታዳጊው ወላጅ አባት አርሶ አደር ቢረሳው ተዋበልኝ ልጃቸውን ለማሳከም ጥሪታቸውን አራግፈዋል፡ ወላጅ አባት እንደሚሉት ለህክምናው ወጭ መሬታቸውንና  ከብቶቻቸውን  ሸጠዋል፡፡

ከሚኖሩበት ጎጃም-አማኑል እየተመላለሱ ለማሳከም ኢኮኖሚያዊ ጫናው ስለከበዳቸው ተስፋ ቆርጠው ህክምናውን ለማቋረጥ ተገደው እንደነበር ያስታወሱት የአባይነህ ወላጅ አባት  በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ በተደረገላቸው ድጋፍ ህክምናውን ሊቀጥሉ እንደቻሉም ይናገራሉ፡፡

ካንሰር  የታመመ  ህጻን  ልጃቸውን  ለማሳከም   ከቤተሰብ ርቀው  በሚያደርጉት  ውጣ ውረድ ለከፍተኛ እንግልት እንደተዳረጉ  የሚናገሩት  ደግሞ  ከቦረና መካነ ሰላም የመጡት ወ/ሮ ኒአቢን ሰልማ  የተባሉ እናት ናቸው፡፡

ወ/ሮ ኒአቢን  እንደሚሉት የአልጋ፣ የምግብ፣ መድሃኒት  ወጭ ከፍሎ ማሳከም በእግጅጉ አስቸጋሪ  ሆኖባቸዋል፡፡ በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ በተደረገላቸው ድጋፍ  የልጃቸውን  ህክምና ለመከታተል ችለዋል።

የማቲወስ ወንዱ የኢትጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የህሙማን እንክብካቤ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ሞገስ እንደሚሉት ህሙማን ለህክምና በሚሰጣቸው ረዥም የጊዜ ቀጠሮ ተስፋ ቆርጠው ወደ ሃገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ብዙ ነው። ህሙማኑ ቀጠሯቸው እስኪደርስ በመጠባበቅ ላይ እያሉ ተራ ሳይደርሳቸው  ለህልፈተ ህወት የሚዳረጉበት አጋጣሚ መኖሩንም ይናገራሉ፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የስነ ካንሰር ህክምና ክፍል ሃላፊው ዶክተር አይናለም አብረሃ እንደሚሉት የካንሰር መነሻው የሰውነት ህዋሳት በሆነ ምክንያት ከህግጋት ውጭ በሆነ መንገድ ሲራቡ ነው፡፡ ከበሽታው መንስኤዎች መካከል የእድሜ መግፋት፣ የአመጋገብ ስርዓት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ለሱስ  ተጋላጭነት፣ የምንኖርበት አካባቢ፣ በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ ተጠቃሽ መሆናቸውን ሙያዊ ማብራሪያ ይሰጣሉ።

                          የካንሰር  ህክምና እንዴት ይሰጣል?

የካንሰር በሽታ ህክምናው በቀዶ ህክምና፣ በኬሚካል፣ በጨረር፣ በተናጠል  ወይም በጥምረት ሊሰጥ እንሚችል ዶክተር አይናለም ያብራራሉ፡፡ የቀዶ ህክማናው በማንኛውም ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ካለ ሊሠጥ እንደሚችልም ይናገራሉ፡፡ የኬሚካል ህክምና- የኬሞ ቴራፒ በመድሃኒት መልኩ እንደሚሰጥ የተናገሩት ዶክተር አይናለም በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ በሃዋሳ፣ በመቀሌና በጎንደር  እየተሰጠ ነው።

በሽታው  ታክሞ የመዳን  እድሉ  በካንሰሩ አይነት፣ ህክምናው የተሰጠበት ወቅት ማለትም  በሽታው ሳይባባስ  ህክምና ከተጀመረ የመዳን እድሉ ሰፊ መሆኑና ተሰራጭቶም የተሟላ ህክምና ከተደረገ ሊድን እንደሚችል  ከዶክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ችለናል፡፡         

                           የታመመ ሰው ለምን ለአመት ይቀጠራል ?

ንሰር በሽታን ለማከም  የጨረር ህክምና  በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ከመሰጠቱም ባለፈ በሆስፒታሉ የጨረር ህክምና መስጫ ማሽን አንድ ብቻ መሆኑና ከህክምናው ፈላጊዎች ቁጥር ጋር ባለመጣጣሙ  ህሙማን ረዥም የጊዜ ቀጠሮ ለመጠበቅ  እንደሚገደዱ ነው ዶክተር ዓይናለም የሚናገሩት። የህክምና መሳሪያ አቅርቦት፣ በህክምናው የሰለጠነ  በቂ የሰው ሃይል አለመኖር ፣ የህክምናው  ተደራሽነት  ውስንነ መሆን ህክምናውን  ከባድ አድርጎታል፡፡

በኢንተርናሽናል የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቀመር መሰረት ለአንድ100 ሚሊየን ህዝብ 100 ማሽን እንደሚያስፈልግ ያስቀምጣል የሚሉት ዶክተር ዓይናለም ኢትዮጵያ አሁን ላላት  የህዝብ ቁጥር በአንድ ማሽን ብቻ አገልግሎቱን ሰጥቶ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡

ችግሩን ለማቃለል የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን የሚያብራሩት ዶክተር አይናለም በቅርቡ ማሽኖች ተገዝተው ሥራ ለማስጀመር የመገጣጠም ሥራ እየተሰራ  ነው ይላሉ።  የህክምናውን ተደራሽነት ለማስፋትም እንቅስቃሴ መኖሩን ያነሱት ዶክተሩ ከተሳካ ከወራት  ወይም ከአመት በኋላ ህክምናው በሃረማያ፣ ጅማ፣ በጎንደር ና በመቀሌ ሊሰጥ እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡

በዘርፉ በቂ የህክምና ባለሙያ አለመኖሩ ሌላኛው ችግር በመሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉን ባለሙዎች እያሰለጠነ ስለሆነ ከምስት አመት በኋላ በሀገሪቱ ከ50 እስከ 60 የሚደርሱ የስነ ካንሰር ስፔሻሊስቶች ሊኖሩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡ 

ዶክተሩ በሆስፒታሉ ስለሚሰጠው የህክምና አገልግሎት በተለይ ስለካንሰር ህክመና ሲናገሩ ህሙማን በማታው የህክምና አገልግሎት እንዲታከሙ ሆነ ብለው የሚገፋፋ ሃኪሞች ይኖራሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው እና ከነጭራሹም አገልግሎቱ ለጊዜው መቋረጡን ነው የሚጠቅሱት።

በማታው የህክና አገልግሎት ለመታከም እስከ አራት ወራት የሚደርስ ወረፋ መጠበቅ ግድ የሚል ቢሆንም  አገልግሎች አሰጣጡ ብዙም ከመደበኛው አይለይም ይላሉ።

የህክምና ባለሙያውም ቢሆን ሰው እንደመሆኑ መጠን በሚያየው ነገር ያዝናል፣ሰው ታሞ ልትረዳው እየቻልክ  በሁኔታዎች አለመሟላት ሳይታከም ሲቀር የሚሰማንን ስሜት በቦታው ስትሆን ብቻነው የምታውቀው ይላሉ ዶክተሩ። ይህ ቢሆንም ከታካሚው ጋር አብሮ በማልቀስ  ታማሚውን የበለጠ ችግሩን ማባበስ ሙያው አይፈቅድም ያሉት ዶክተር ዓይናለም በሙያዊ ስነ-ምግባር መሰረት ህሙማንን ማጽናናት እንደሚገባም ያምናሉ።  

                             መከላከያውስ?

ህብረተሰቡ  ስለካንሰር  በሽታ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ፣ ሴቶች ጡታቸውን በወር አንድ ጊዜ ቢታዩ፤ አለፍ  ሲልም ጡትን  በእጅ በመንካት የተለየ ነገር ካለ ወዲያው መመርመር ቢችሉ ፣  የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መግባት የካንሰር ምልክት ሊሆን ስለሚችል  ወደ ህክምና መሄድ  እንደሚስፈልግ  ምክራቸውን  የሚለግሱት ደግሞ  የውስጥ  ደዌና የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር ቦጋለ ሰለሞን ናቸው ።

እነዚህ በሽታዎችን ለመከላከል የአመጋገብና የአኗኗር ዘይቤያችንን በማስተካከል እንዲሁም አጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች እራስን በማራቅ ከመሰል የውስጥ ደዌ በሽታዎች የመያዝ እድልን መቀነስ እንደሚቻልም ባለሙያዎቹ ያብራራሉ።  

ስለበሽታው የህብረተሰቡ  ግንዛቤ  በአንጻሩም ቢሆን መሻሻል እያሳየ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር ቦጋለ  አሁንም  ህብረተሰቡ፣ መንግስት፣  የሚዲያ ተቋማትና ሌሎች የባለድርሻ  አካላት ግንዛቤ በመፍጠር በኩልና በሽታውን ለመከላከል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ  ሊወጡ ይገባል ይላሉ።  ሰላም! ጤና ይስጥልኝ ጤናዎትን ያብዛሎት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም