የኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አጎራባች ህዝቦች የሰላም ኮንፍረንስ አካሄዱ

92

ነቀምቴ መጋቢት 12/2011  ሰላማቸውን የሚያውኩ ግለሰቦችን አጋለጠው ለህግ እንዲቀርቡ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አጎራባች አካባቢ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

የሁለቱ አጎራባች አካባቢ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ህዝባዊ የሰላም ኮንፍረንስ ዛሬ   በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ ተካሄዷል፡፡

ከኮንፍረንስ ተሳታፊዎች መካከል የባምባሲ ወረዳ ነዋሪ  ወይዘሮ መነን አሊ በሰጡት አስተያየት የአካባቢያቸውን ሰላም ለማወክ  የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን አጋልጠው ለህግ እንዲቀርቡ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

" የኦሮሞና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝብ አንድ ቤተሰብ" ናቸው ያሉት አስተያየት ሰጪዋ  የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሊያጋጯቸው የሚሞከሩ ኃይሎችን ስርዓት ለማሲያዝ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡

የፀረ ሰላም ኃይሎች አፍራሽ ሴራ በማክሸፍ የነበረውን ሰላም ለማስመለስ የሰላም ኮንፈረንሱ ሚና የጎላ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በጊ ወረዳ የተሳተፉት ቄስ ወንድሙ መሃመድ ናቸው፡፡

ሰላማቸውን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ  ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በአሶሳ ዞን የባምባሲ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ ሙሳ ሳድቅ በበኩላቸው የኦሮሞና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች  መለያየት የማይችሉ የተሳሰሩ እንደሆኑ ገልጸው  የጋራ ጥቅማቸውን ለማስከበር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የሁለቱ ክልል ህዝቦች ሰላም በጋራ ተጠብቆ በፍቅር እንዲኖሩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ ዘሪሁን ተክሉ  ናቸው፡፡

የኦሮሚያና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ደሳለኝ  የሰላም ኮንፈረንሱ ለአምስተኛ ጊዜ መካሄዱን ጠቅሰው እስካሁን በሁለቱም ክልልች ከ40 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደነበሩበት ቄዬ መመለሳቸውን አስታውቀዋል።

የሁለቱም ክልል ህዝቦች የተላላኪ አጥፊዎችን መረብ በመበጣጠስ አንድነታቸውንና ፍቅራቸውን በማጠናከር የአካባቢያቸው ሰላም ማስጠበቅ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

የ22ኛው መከላከያ ሰራዊት አዛዥ ኮሎኔል አማረ ሞላ  ወንጀለኞችን ወደ ህግ ለማቅረብ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ሁለቱ አጎራባች  ህዝቦች ከፀጥታ ኃይሎች ጎን በመቆም የአካባቢያቸውን ሰላም  መጠበቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ተመሳሳይ የሰላም ኮንፍረንስ  በምስራቅ ወለጋ ሳሲጋ ወረዳ በሎ ከተማ ዛሬ የተካሄደ ሲሆን በሁለቱም ስፍራዎች ከየአካባቢው የተወጣጡ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣  አባገዳዎች፣ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም