ኢትዮጵያና ሩሲያ ካላቸው የእድገት ራዕይ አንፃር ተደጋግፈው የሚሰሩበት ጊዜ አሁን ነው—በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር

761

አዲስ አበባ  መጋቢት 12/2011 “ኢትዮጵያና ሩሲያ ካላቸው የእድገት ራዕይ አንፃር ተደጋግፈው የሚሰሩበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ቪዝቦልድ ከቺንኮ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ቪዝቦልድ ካቺንኮን አሰናብተዋል።

ፕሬዚዳንቷ ከሩሲያው አምባሳደር ጋር በነበራቸው የስንብት ፕሮግራም ወቅት ስለነበራቸው ቆይታና ስለ ቀጣይ የሁለቱ አገራት የግንኙነት ራዕይ ተወያይተዋል።

ከውይይቱ በኋላ የሩሲያ አምባሳደር ቪዝቦልድ ከቺንኮ እንደገለጹት፤ ወቅቱ ሁለቱ አገሮች የበለጠ ትብብራቸውን የሚያጠናክሩበት ነው” ሲሉ አምባሳደሩ ከውይይቱ በኋላ ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት በአሁኑ ወቅት በጥሩ እድገት ላይ ከመሆናቸውና ካላቸው የእድገት ራዕይ አኳያ እውቀትና ተሞክሮ መመጋገብ የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የመጣውን አጠቃላይ ለውጥ ያደነቁ ሲሆን በተለይ የአገሪቱን መፃኢ የፖለቲካ እድል ለማስተካከል በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመክሩ እድል መፈጠሩ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

”በመናገርና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ የመጣው መሻሻል ጥሩ ነው” ያሉት አምባሳደሩ ለውጡ እንዲቀጥል መንግስት ሁሉንም ዜጎች ባካተተ መንገድ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በተያያዘ ዜና ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በኢትዮጵያ ቫቲካን ሲቲ ስቴትን ወክለው ለሶስት አመት ያገለገሉትን አምባሳደር ሉጂ ቢያንኮን ያሰናበቱ ሲሆን ሁለቱ አገሮች ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።

ቫቲካን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኩል ለኢትዮጵያ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች የማህበራዊ ድጋፍ ስታደርግ የቆየች ሲሆን ይህንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል።