በጅማ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ አካላት ላይ ቅሬታ ቀረበ

65

ጅማ መጋቢት 12/2011 የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ አካላት አለአግባብ እየቀጧቸው መቸገራቸውን በጅማ ከተማ  የታክሲ ባለንብረትና አሽከርካሪዎች ቅሬታቸው ገለጹ፡፡

በወቅታዊ የትራንስፖርት አገልግሎት  አሰጣጥ፣ የባለንብረቶችና የአሽከራካሪዎች መብትና ግዴታ ዙሪያ በጅማ ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡

ከውይይት ተሳታፊዎች መካከል የሚኒባስ አሽከርካሪው  አቶ አቤነዘር እሱእንዳለ በሰጡት አስተያየት "  ህግና ደንብ አክብረን እያሽከረክርን ባለንበት ሰዓት ፈልገው የሚቀጡን የትራፊክ ፖሊሶች በሰሞኑ ዘመተውብናል " ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስበብ አስባቡ የመቅጣቱ ሁኔታ በመብዛቱ ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

የታክሲ ባለንብረት የሆኑት አቶ ከድር መሃመድ በበኩላቸው " ምንም ባልተላለፍኩት ድንብ ዘጠኝ መቶ ሃያ ብር ቅጣት እንድክፍል ተደርጊያለሁ" ብለዋል፡፡

ቅጣቱም እንዲነሳላቸው ለሳምንታት አቤቱታ ቢያቀርቡም ሰሜ እንዳላገኙ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ኑሮና የመለዋወጫ እቃ  በተወደደበት ሁኔታ  አግባብነት የሌለው ቅጣት መብዛት  ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

የትራፊክ ፖሊስ  ከመስመርህ ውጭ በመስራት በሚል ስበብ አምስት መቶ ብር እንዲቀጣ እንደወሰነበት የገለጸው ደግሞ የባጃጅ አሽከርካሪው  ወጣት ካሳሁን በላቸው ነው፡፡

"ጉዳዩን ለማስረዳት ስሞክር አመናጨቀኝ ፤ያልተገባም ስድብ ሰደበኝ"  ሲል ቅሬታውን  አቅርቧል፡፡

የጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮማንደር አበዱረዛቅ ነጋ ባለፈው ወር በከተማው የትራፊክ አደጋ በመብዛቱ ምክንያትና በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ህብረተሰቡ ያነሳውን ቅሬታ ተክትለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት  ቁጥጥራቸውን ማጠናከራቸውን ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት ባለንበረቶችና አሽከራካሪዎች ከተለመደው ውጭ በመጫን፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፍልና ሌሎችን የህግ ጥሰቶችን እየፈጸሙ በመገኘታቸው ይህንን  ለማስተካከል እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

" በዚህ አጋጣሚ የስነ ምግባር  ችግር ያለባቸው  አይኖሩም ብሎ መከራከር እይችሉም፤  በእናንተ ውስጥም በእኛም ችግር ፈጣሪዎች እንደሚኖሩ መገንዘብ አስፈላጊ ነው " ብለዋል፡፡

በደል ያደረሱ የትራፊክ ፖሊሶችንና ተቆጣጣሪ ባለሙያዎችን አጣርተው አስፈላጊውን አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ አዛዡ አስታውቀዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላትም የህግ የበላይነት እንዲከበር ከመጠይቅ ባለፈም በማስጠበቅ የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጅማ ከተማ ትራንስፖርት ባለስልጣን የትራንስፖርት አቅርቦት አገልግሎት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ረሻድ አባቢያ በበኩላቸው በከተማው ተቆርጦ የነበረው የሚኒባስ ታክሲ አገልግሎት ከመጋቢት10/2011ዓ.ም. አንስቶ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ በከተማው የሚገኙ የሚኒባስ ታክሲና የባጃጅ ባለንብረቶች፣አሽከርካሪዎች ፣የትራንስፖርት ባለንበረቶች ማህበርና አስፈጻሚ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በጅማ ከተማ ከመጋቢት 9/2011ዓ.ም.  ጀምሮ  የሚኒባስ ታክሲ አገልግሎት በመቋረጡ እንደተቸገሩ  ነዋሪዎች መግለጻቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል፡፡

በከተማውም የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አራት መቶ ሰላስ አምስት ታክሲና 1ሺህ 220 የባለሶስት እግር ባጃጆች እንደሚገኙ ከከተማ የትራንስፖርት ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም