የለውጡ ሂደት እንዳይደናቀፍ ህዝቡ በአንድነቱ ጸንቶ መታገል አለበት--አንድነት ፓርቲ

65

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 የለውጡ ሂደት እንዳይደናቀፍና የህግ የበላይነትን እንዲከበር ህዝቡ በአንድነቱ ጸንቶ መታገል አለበት ሲል አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ /አንድነት/ ፓርቲ አሳሰበ።

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ትዕግስቱ አወል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግስትም የህግ የበላይነት እንዲከበር አፋጣኝ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የፖለቲካ አለመረጋጋት እንደሚስተዋልና በዚህም ሳቢያ የዜጎች መፈናቀልና ስደት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል።

''መንግስት መረጋጋትን በማስፈን ሰላም እንዲረጋገጥ ከሁሉም የክልል መንግስታት ጋር  በመነጋገር ችግሩን በፍጥነት ማስቆም አለበት'' ብለዋል።

እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻለና ግጭቶች ከቀጠሉ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ቀርቶ አገሪቷ እንደ አገር የመቀጠል ህልውናዋን ይፈታተናል ። 

ስለዚህ መንግስት ለህግ የበላይነት መከበር የሚፈለገውን ዋጋ ከፍሎ ዜጎች በፈለጉት ክልል የመንቀሳቀሰ መብታቸውን ለማስከበር ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

አንዳንድ ህገወጦች በለውጥ ስም የህግ የበላይነትን ወደ ጎን በመተው ህዝቡ በአንድነቱ የፈጠረውን ኢትዮጵያዊነት በመፈታተን ላይ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

''ህብረተሰቡም  ወጣቶችን በማደራጀት  አገርን ለማተራመስ የሚጥሩ ህገወጦችን በንቃት በመከታተል  ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግና የአገሩን አንድነት መጠበቅ አለበት'' ብለዋል።

አዲስ አበባ  የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ የሚነሳባት ጥያቄ በህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት እንዲፈታ ፓርቲው ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም