ኧረ ከኬንያ እንማር ጎበዝ!

76

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 በኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት አንጻር መገናኛ ብዙሃን የጥላቻ ጥይት የሚተኮሱባቸው አውድማዎች ከሆኑ ሰነባብተዋል።

መገናኛ ብዙሃን ዜጎችን በቡድን የሚከፍሉ  አጀንዳዎችን የተሸከሙ ግለሰቦች እንደፈለጉ የሚፈነጩባቸውና ሃይ ባይ የሌላቸው ተቋማት እየሆኑ መምጣታቸውን ለመረዳት መንግስት ጉዳዩን ለመግታት   የሚያወጣቸውን መግለጫዎች ማየት በቂ ነው።

ከዚህ ቀደም ይህ ተግባር የማህበራዊ ሚዲያዎች መገለጫ የነበረ ሲሆን፤  ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ተዛምቶ የ "እኛ እና እነሱ" ትርክት የእለት ተእለት ደወል ሆኗል።

"ሳይቃጠል በቅጠል" እንዲሉ የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ቶሎ ፈር ካልተበጀለት ኢንዱስትሪውን ሊቀላቀሉ ያሰቡ ተቋማት ከወዲሁም በምን መልኩ ሊዘጋጁ አንደሚችሉ መገመት አያዳግትም።

በአንጻሩ ጎረቤት አገር ኬኒያ አኛን ከሚያስጨንቀን የመገናኛ ብዙሃን አፈንጋጭነት በጊዜ ተላቃለች።

ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ኢንዱስትሪውን የሚመራ ጠንካራ 'የሚዲያ መማክርት (ካውንስል)' ማቋቋም መቻሏ ነው።

የኬንያ የሚዲያ መማክርት እ.አ.አ በ2004 የተለያዩ የግል ሚዲያ ተቋማትና ማህበራት በጋራ ያቋቋሙት ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ከመንግስት ድጎማ እስከማግኘት የደረሰ ተጽእኖ ፈጣሪ ተቋም ሆኗል።

ተቋሙን ለአምስት ዓመታት በዋና ስራ አስፈጻሚነት ያገለገሉት ዶክተር ሐሮን ማውንጊ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ መማክርቱ ከመቋቋሙ በፊት በአገሪቷ ውስጥ ያሉ የሚዲያ ተቋማት "ያልተደራጁና እርስ በርስ የሚጋጩ" ነበሩ።

ከዚህ አንጻር ኬንያውያን በኢንዱስትሪው ላይ እምነት እንዳልነበራቸው በማውሳት።

የሚዲያ መማክርት መቋቋሙ ሃሳባቸውን ነጻና ገለልተኛ ሆነው ህዝብን የሚያገለግሉ መገናኛ ብዙሃንን ከመፍጠር ባለፈ የሚነሱ ቅሬታዎችን በወቅቱ መፍታት መቻላቸውን አውስተዋል።

ይህን በማድረግም መገናኛ ብዙሃንን በኬንያውያን ዘንድ ግንባር ቀደም ተዓማኒ ተቋም አድርገነዋል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚዲያ መማክርት አለመኖር ጫፍና ጫፍ የረገጡ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እንዲበራከቱ አድርጓል ይላሉ።

ይህ ደግሞ የጋዜጠኞች አቅም ይጎለብት የነበረበት እድል ማሳጣቱንም አክለዋል።

አሁን ላይ መንግስት ለሚዲያው የተሻለ ነጻነት መስጠቱን ጠቁመው፤ ይህን እድል በመጠቀም በማህበረሰቡ ዘንድ እፎይታን የሚፈጥር ጠንካራ የሚዲያ መማክርት ለመቋቋም ማዋል እንደሚገባ መክረዋል።

በአሁኑ ወቅት በኬንያ ቁጥራቸው ከሰባ በላይ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲኖሩ፤ መቀመጫቸውን ናይሮቢ ያደረጉ የሬዴዮ ጣቢያዎች ብቻ ከአንድ መቶ በላይ መድረሳቸውን ከኬንያ ሚዲያ መማክርት ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም