ፍኖተ ካርታው የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ችግሮችን ይፈታል—ትምህርት ሚኒስቴር

678

መቀሌ መጋቢት 12/2011 የትምህርት ፍኖተ ካርታ በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ያሉትን ችግሮች ከመፍታት ባለፈ ግብረ-ገብነትን የተላበሰ ትውልድ ለመቅረጽ  የሚያስችል መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላየ ጌቴ አስታወቁ።

ሁለም ክልሎችና ሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች የተሳተፉበት 28ኛው የትምህርት ጉባኤ በመቀሌ እየተካሄደ ነው፡፡

በጉባኤው ላይ ፍኖተ ካርታው ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሁሉም የትምህርት እርከኖች የሚሰጠው ትምህርት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ እንደተናገሩት ስራ ላይ ያለውን የትምህርት መዋቅርና ስርአተ ትምህርት ለማሻሻል በርካታ ምክር ሀሳቦች ተሰብስበዋል።

ትውልዱ እርስ በራሱ እንዲፋቀር፣እንዲከባበርና አብሮነቱን እንዲያጠናክር ግብረ-ገብነትን መማር አለበት የሚል ሀሳብ ሁሉም መድረክ የተስማማበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“ትውልዱ ለደረጃው የሚመጥን እውቀትና ክህሎት እየያዘ ባለመሆኑ የምዘና ስርአቱ እንዲቀየር ከተገኙ ምክረ ሀሳቦች ውስጥ የሚካተት ነው” ብለዋል፡፡

“ባለፉት ዓመታት የተሰጠው ትምህርት ማንነትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ አሁን ማንነትና ኢትዮጵያዊነትን የተቀበለ ሁለቱንም ያመጣጠነ ስርዓተ-ትምህርት እንዲቀረጽ ከምክረ ሀሳቡ ተገኝቷል” ብለዋል፡፡

ተማሪዎቹ አሁን የ10ኛ ክፍል ትምህርት የሚያጠናቁቁበት እድሜ በአእምሯቸውና በአካላቸው ለስራ ብቁ ያልሆንበት በመሆኑ እንዲቀየር በሁሉም መድረክ አንድ አይነት ሀሳብ መቅረቡንም ተናግረዋል፡

“እስከ አሁን ግርታ እየፈጠረ ያለው ልጆች ስምንተኛ ክፍል ላይ አንድ አይነት ፈተና ይወስዳሉ ሲባል ሁሉም ህጻናት በአንድ አይነት ቋንቋ ይፈተናሉ ማለት አይደለም” ብለዋል።

“ፍኖተ ካርታው ህጸናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ይበልጥ ያጠናክር ይሆናል እንጂ አሁን ወደ ሃላ የሚመለስ ነገር የለም” ብለዋል።

የአገሪቱ የትምህርት አመራርና ስልጠና ከፖለቲካ ጋር ሳይቀላቀል ይህንን ፍኖተ ካርታ ማስተግበር የሚችል ከታች እስከ ሚኒስትር እየተደረጃ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የትምህርት ጥራት ተቆጣጣሪና ስርአተ ትምህርት ምዘናና አዘጋጆች አንድ ጋር የተቀላቀሉ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ “ይህም ተጠያቂነት ባለው መንገድ መለወጥ አለበት ብለን አቋም ይዘናል” ብለዋል፡፡

በሌላው የክርክር ሃሳብ ተማሪዎች ትምህርት የሚጀምሩበት እድሜ ሶስት አማራጮች መቅረባቸውን የገለጹት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጽሕፈት ቤት አማካሪ አቶ ከፍያለው አያሌው ናቸው፡፡

“ምክረ ሀሳቦቹ ህጸናት በስድስትና በሰባት ዓመት ወይም በከተማና በገጠር ተብሎ በሁለቱም የእድሜ ደረጃ ትምህርት እንዲጀምሩ የሚሉ ናቸው” ብለዋል፡፡

ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ በሁለት ቀናት ቆይታው በቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ላይ አቋም በመያዝ ለውሳኔ ሰጪ የመንግስት አካል እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡