ለረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም ዝቅተኝነት ተጠያቂ አካል ሊኖር ይገባል ተባለ

87

አዲስ አበባ  መጋቢት 12/2011 ለረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ዝቅተኛ አፈጻጸም ተጠያቂ አካል ሊኖር እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ።

'በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው' የተባለው ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በነሃሴ ወር 2010 ዓ.ም. በይፋ ቢመረቅም እስካሁን ድረስ ኃይል ማመንጨት አልጀመረም።

የፕሮጀክቱ ግንባታ በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ ተጠናቆ አገልግሎት ይሰጣል ቢባልም ባጋጠመው ችግር ኃይል ሳያመነጭ ቆይቷል።

120 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 50 ሜጋ ዋት ሃይል እንደሚያመነጭ ቢታቀድም  የኋላ ኋላ የዲዛይን ለውጥ በማድረግ 25 ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ ተደርጎ ተገንብቷል።

ይሁንና የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ስራው ሳይጠናቀቅ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ ቢባልም ኃይል ማመንጨት ግን አልቻለም።

ይህን ተከትሎ ዛሬ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ8 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት በኤሌክትሪክ ታዳሽ ሀይል ዘርፍ ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም 95 ነጥብ 65 በመቶ መድረሱን አስታውቋል።

ይሁን እንጂ የምክር ቤቱ አባላት ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ከተባለለት ጊዜ ገደብ ለሁለት ዓመታት መዘግየቱን በመጥቀስ የህዝብና የመንግስት ሀብት በመባከኑ ተጠያቂ አካል ሊኖር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የውሃ፣ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፤ በፕሮጀክቱ ዙሪያ ያለውን ክፍተት ለማጣራት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።

ለችግሩ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን በውል ስምምነት ላይ የነበሩ ክፍተቶችን አንስተው ለአብነትም የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ከ50 ሜጋ ዋት ወደ 25 ሜጋ ዋት እንዲወርድ መደረጉንም አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ አሁን ላይ መንግስትን 10 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወጪ መዳረጉን የገለፁት ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እየተሰራ እንደሆነና ለክፍተቱ ምክንያት የሆኑትን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም