ኡጋንዳ በዋትስአፕ ተጠቃሚዎች ላይ የታክስ ህግ አወጣች

76
ግንቦት 23/2010 ኡጋንዳ በዋትስአፕ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ተጠቃሚዎች ላይ በየቀኑ ታክስ ለመቁረጥ የሚያስችላትን ህግ ይፋ አደረገች። የመልዕክት መለዋወጫ አገልገሎት የሚሰጠውን ዋትስ አፕ መተግበሪያ የሚጠቀሙ ኡጋንዳውያን በየቀኑ 200 ሺልንግ ወይም 0 ነጥብ 05 ዶላር ታክስ ይቆረጥባቸዋል። ይህን ማድረግ የሚያስችለውን አወዛጋቢ ህግ የሀገሪቱ ፓርላማ አፅድቆታል። ከመጪው የፈረንጆቹ ሃምሌ 1 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፥ ከዋትስአፕ በተጨማሪ እንደ ፌስቡክ ያሉ መተግበሪያዎችን የሚቀጠሙት ላይም ታክስ ይቆረጣል ነው የተባለው። በወጣው ህግ መሰረት በሀገሪቱ በሞባይል የሚፈፀም ግብይት 1 በመቶ ታክስ ይጣልበታል። የአሁኑን የኡጋንዳ እርምጃ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትን ለማፈን የታሰበ ነው ብለውታል። ከፓርላማ አባላት መካከል ቢያንስ ሶስት ያህሉ አዲሱ ህግ በተጠቃሚዎች ላይ ተደራራቢ ታክስ የሚጥል ነው በሚል ተቃውመውታል። አባላቱ ኡጋንዳውያን ዋትስአፕን የሚጠቀሙት ታክስ በሚቆረጥበት የአየር ሰዓት መሆኑን አንስተው፥ የአሁኑ ታክስ ደግሞ ተጨማሪ በመሆኑ መብታቸውን የተጋፋ ነው ብለዋል። ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችንም እንደሚጎዳ ነው ያነሱት። የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ባለፈው ወር በሀገሪቱ የማህበራዊ ትስስር ገፆች በዋነኛነት እያገለገሉ ያሉት ለጭምጭምታ መረጃዎች ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ምንጭ፦ቢቢሲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም