ኢትዮ-ቴሌኮም ለተፈናቀሉ ወገኖች 40 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

97

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2011 ኢትዮ-ቴሌኮም ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማሰባሰቢያ የሚውል አጭር የፅሁፍ መልዕክት ቁጥርና የ40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

ኩባንያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የገንዘብ ድጋፉና ለገቢ ማሰባሰቢያ የሚውል አጭር የፅሁፍ መልክት ቁጥር ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና በመንግስት እየተደረገ ያለውን አገራዊ ጥረት ለማገዝ ነው።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር እያደረጉ ያለውን የድጋፍ እንቅስቃሴ በተቀናጀ መልኩ ለማካሄድ ይረዳ ዘንድ 6020 አጭር የፅሁፍ መልክት ቁጥር ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

በመሆኑም መላው ህብረተሰብ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት 'በ6020 ላይ A' ብለው በመላክ በአንድ መልእክት 2 ብር ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ አስታውቋል።

በዚህ መልክ የሚሰበሰበውን ገንዘብም ለፌዴራል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ስራ አመራር ኮሚሽን የሚያስረክብ መሆኑንና የሚሰበሰበው ገንዘብ አስመልክቶ ለህብረተሰቡ በየጊዜው መረጃ እንደሚሰጥ ገልጿል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ለተፈናቀሉ ዜጎች ያደረገውን የ40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለፌዴራል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ስራ አመራር ኮሚሽን ማስረከቡን በላከው መግለጫ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም