በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቀሌ ቅርንጫፎች አገልግሎት ቀልጣፋ አለመሆን ቅሬታን ፈጥሯል

85

መቀሌ መጋቢት 12/2011 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቀሌ ከተማ በሚገኙ ቅርንጫፎች የሚሰጠው አገልግሎት ቀልጣፋ ባለመሆኑ መጉላላት እንደገጠማቸው የባንኩ ደንበኞች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡

ችግሩን ለመፍታት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑነን በባንኩ የመቀሌ ዲስትሪክት አስታውቋል፡፡

ከባንኩ  ደንበኞች መካከል  አቶ ምሩፅ ኃይለስላሴ  ለኢዜአ እንደገለጹት ቅርንጫፎቹ  የተቀላጠፈ አገልግሎት ስለማይሰጡ  ወረፋ ይዘው ለሰዓታት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡

የባንኩ የውስጥ ክፍል በተገልጋዮች እየሞላ መንገድ ድረስ ወረፋ የሚዙበት አጋጣሚ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

የንግድ ባንክ አገልግሎት ለማግኘት ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ወረፋ ለያዝ የሚገደዱበት ሁኔታ እንዳለ አመልከተው  በተደጋጋሚ ችግሩ ከሚስተዋልባቸው መካከል የሃወልትና መሰቦ  ቅርንጫፎች እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡

" በየቅርንጫፎቹ  እስከ አስር የሚደርሱ የአገልግሎት መስጫ መስኮቶች ቢኖሩም በተግባር ግን አገልግሎት የሚሰጡ  ከአራት አይበልጡም" ብለዋል፡፡

በባንኩ ዓዲሽምድሁን   ቅርንጫፍ በወረፋ መብዛት ምክንያት እንደሚጉላሉ  የተናገሩት ደግሞ  ሌላው ደንበኛ ሲስተር ሃደስ አብረሀለይ ናቸው፡፡

በወረፋ መብዛት ምክንያት ደመወዛችን በወቅቱ ለማውጣት እንደሚቸገሩም ጠቁመዋል፡፡

የንግድ ባንክ አገልግሎት አስር ሰዓት ተኩል አገልግሎታቸው የሚያቆሙ በመሆናቸው መንግስት ሰራተኛው እንግልት እንደሚገጥመው  አመልክተዋል፡፡

በንግድ ስራ የተሰማሩት  አቶ ጌታቸው ፀጋይ በሰጡት አስተያየት የንግድ ባንክ የኢቲኤም  ማሽኖችም ሲበላሹ በፍጥነት ስለማይስተካከሉ  እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡

ስለጉዳዩ የተጠየቁት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት  ኦፕሬሽንና ሎጀስቲክስ ስራ አስከያጅ አቶ መስፍን ሃጎስ  ደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ከማግኘት ጋር በተያያዘ ያቀረቡት ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

" የችግሩ ምክንያት በትግራይ ክልል በሚገኙ በ105 ቅርንጫፎች ባለፈው ዓመት ከነበረው ከ1ነጥብ 3 ሚሊዮን የተገልጋዩ ብዛት አሁን ወደ 1ነጥብ4 ሚሊዮን ከፍ በማለቱ ነው"ብለዋል።

አቶ መስፍን እንዳመለከቱት የመብራት መቋረጥ ሲያጋጥም ባንኩ የሚጠቀምባቸው ጀነሬተሮች አውቶማቲክ  ባለመሆናቸው ምክንያት በሰው ኃይል ጀነሬተሮችን እስኪ ነሱ መዘግየት ያጋጥማል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታትም እስከመጪው  ሰኔ ወር ድረስ 11 ተጨማሪ ቅርንጫፎች እንደሚከፈቱ ጠቁመው  ባንኩ  በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ሁሉም ተገልጋይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ያለ ምንም ወረፋ 24 አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም