የአክሱም ሐውልትን ከጉዳት ለመታደግ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው - ነዋሪዎች

131

አክሱም መጋቢት 12/2011 የአክሱም  ሐውልትን ከጉዳት ለመታደግ  የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በሐውልቱ እድሳት ዙሪያ የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ  የስራ ኃላፊዎች ጋር ትናንት ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ነዋሪዎቹ እንዳሉት   የመውደቅ አደጋ ስጋት የተደቀነበትን  ሦስተኛውን  የአክሱም ሐወልት ለመታደግ በሚኒስቴሩ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው።

ከውይይቱ  ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ያፊት ታደሰ አለም አቀፍ እውቅና ያለው ወጥ ሐውልት  በጸሐይና ብርድ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመመ መምጣቱን ተናግሯል።

ለሐወልቱ ተገቢው ጥገና እንዲደረግለት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተደጋጋሚ ጥያቂዎች ቢቀርብለትም  ጥናት ላይ ነን ከሚል ውጭ ወደ ተግባር የሚሸጋገር ስራ አለመስራቱን ጠቁሟል።

አቶ አበበ ተጠምቀ የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚላኩ  የስራ ኃላፊዎች ለሐውልቱ ጥገና የሚያስፈልጉ ዝርዝር ጥናቶች እየተጠኑ ነውና ለጥገናው የሚውል በጀት ተመድቧል ከሚል ያለፈ ተጨባጭ  ስራ እንዳልተሰራ አስረድተዋል።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸሐየ አስመላሽ  ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት ገናና ታሪኮቿ መካከል የአክሱም ሐውልት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።

"የጥንት አያቶቻችን ሰርተውና በክብር ጠብቀው ያቆዩልንን ሐውልት እኛ የአሁኑ ትውልዶች አፍራሾች መሆን የለብንም" ያሉት ፕሬዚዳንቱ  የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ ለሐውልቱ ጥገና ሊያደርግና ለትውልድ ሊያስተላልፈው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዩኒቨርስቲው  ለጥገናው ስራ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎችን  በመመደብ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ተስፋዬ በበኩላቸው  በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየጊዜው እየተሰጠ ያለው ተስፋ በህብረተሰቡ ዘንድ አመኔታን እያጣ መምጣቱን አስታውሰዋል።

በሚኒስቴሩ ሲሰጥ የነበረው ተስፋ ወደ ተግባር ሊቀየር እንደሚገባ አመልክተዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ዘነበሽ መሰረት በነዋሪዎች የተነሱ ጥያቄዎችና የተሰጡ  አስታያየቶች ተገቢ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መስሪያ ቤታቸው በመጀመሪያው የመቶ ቀናት የተግባር እቅድ ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ለማከናወን  ከያዛቸው ስራዎች መካከል የአክሱም ሐውልትን የመጠገን ስራ አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

ለጥገና ስራው  የሚያስፈልገው ዝርዝር ጥናትና የዲዛይ ሰራ መጠናቀቁን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ በሁለተኛው የመቶ ቀናት እቅድ የትግበራ ምዕራፍ ላይ ሐውልቱን የመጠገን ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

በሚኒስቴሩ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሪክተር አቶ ዮናስ ታደሰ   የሐወልቱ የጥገና ስራ አለም አቀፍ ፈቃድና እውቅና የሚጠይቅ በመሆኑ ጊዜ መውሰዱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የሐውልቱን ጥገና  በፍጥነት ለማስጀመር የሚያስችል ፈቃድ ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት ባህልና  ሳይንስ ድርጅት/ዩኔስኮ/ ፍቃድ መገኘቱን አስታውቀዋል።

ጣልያን ከሚገኘው ላታንዚ ከተባለው አለም አቀፍ የቅርስ ጥገና ተቋም ጋርም የስራ ውል ስምምነት መፈረሙንና  ለጥገና ስራው የሚውል በቂ ገንዘብ መመደቡን  አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም