በቡሬ ወረዳ አርሶ አደሮች ላመረቱት በርበሬ የገበያ ችግር አጋጥሞናል አሉ

46

 መቱ መጋቢት 12/2011 በበርበሬ ልማት ተሰማርተው  በተያዘው ዓመት የተሻለ ምርት ቢሰበስቡም አማራጭ ገበያ በማጣት መቸገራቸውን በኢሉአባቦር ዞን ቡሬ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

አርሶአደሮች ለኢዜአ እንዳሉት በ2010/2011 የምርት ዘመን   ለምርቱ ተስማሚ የአየር ንብረት በመኖሩ ካለፈው የተሻለ ምርት ሰብስበዋል፡፡

ሆኖም  ወደ አካባቢያቸው መጥተው ምርት የሚረከቡ ነጋዴዎች ቁጥር በመቀነሱ  ሌላ አማራጭ  ገበያ ማግኘት አልቻሉም፡፡

ኢማም ሼህ ሙሄ  በወረዳው የቶሊጬካ  ቀበሌ አርሶአደር ሲሆኑ  ዘንድሮ ከ2ሺህ ኪሎግራም በላይ የሚሆን የበርበሬ ምርት ሰብስበው ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡

" ዘንድሮ ያገኘሁት ምርት ካለፈው ዓመት በእጥፍ የበለጠ ነው" ያሉት አርሶአደሩ   በብዛት የሚረከባቸው ባለመኖሩ ሙሉ ለሙሉ ለገበያ ማቅረብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የቀበሌው አርሶአደር ታሪኩ ከበደ  በበኩላቸው የበርበሬ ልማት ከእንክብካቤ እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ አድካሚ ሂደትን አልፈው ቢያመርቱም   በቂ ገበያ እና ተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ኪሎውን  በ75 ብር ለነጋዴዎች ሲሸጡ እንደነበር አስታውሰው  ዘንድሮ ዋጋው በመውረዱ እስከ 60 ብር እያስረከቡ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ይረከቧቸው የነበሩ  ነጋዴዎች ቁጥርም ዘንድሮ በመቀነሱ አማራጭ ገበያ በማጣት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ግብይትና ልማት ባለስልጣን የቅመማ ቅመም ልማት ባለሙያ አቶ ቡላ ገብሬ እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ በዞኑ በበርበሬ ከለማው 5ሺህ 691 ሄክታር መሬት ላይ 121ሺ674 ኩንታል ምርት ተሰብስቧል፡፡

ይህም  ከቀዳሚው የምርት ዘመን  ከ36ሺ ኩንታል በላይ የለማው መሬት ደግሞ ከ3ሺ500 ሄክታር በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ባለፈው የምርት ወቅት ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ በምርቱ ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን አስታውሰው  ዘንድሮ ተስማሚ የአየር ንብረት በመኖሩ አርሶአደሩ በስፋት በልማቱ ተሰማርቶ የተሻለ ምርት እንዳገኘ አስረድተዋል፡፡

አርሶአደሩ ያመረተው በርበሬ   በማህበር ተደራጅቶ ለገበያ እንዲያቀርብ ከዞኑ ንግድና ገበያ ጽህፈት ቤት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ወደ አካባቢው በመምጣት ምርት የሚረከቡ ነጋዴዎች ቁጥር መቀነሱ አልፎ አልፎ ከምርት ጥራት መጓደል ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ባለሙያው እንዳሉት አርሶአደሩ በበርበሬ ምርት ላይ አልፎ አልፎ የሚታየውን ሻጋታ መሰል በሽታን እንዲከላከል ምርት ከሰበሰበ በኋላ በተገቢው ማድረቂያ እና ምርት መያዣ እንዲጠቀም ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡

በኢሉአባቦር ዞን 13 ወረዳዎች አርሶ አደሩ  በየዓመቱ  በርበሬን ጨምሮ የተለያየ ቅመማ ቅመም  ይለማል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም