በቋንቋችን መማርና መዳኘታችን ተጠቃሚ አድርጎናል--በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና በአርጎባ ብሔረሰብ ወረዳ ነዋሪዎች

79
ደሴ ግንቦት 23/2010 መብታቸው ተከብሮ በቋንቋቸው መማርና መዳኘት በመቻላቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንና በደቡብ ወሎ  አርጎባ ብሔረሰብ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ከሚሴ ከተማ  የቀበሌ ስድስት ነዋሪ  አቶ አሊ አባድር ለኢዜአ እንዳሉት ከግንቦት 20 ድል ወዲህ የብሔረሰበች  መብትና እኩልነት ተክብሮ ለፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው የአካባቢያቸውን ባህልና ታሪክ እንዲያውቁና ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተከባብረው እንዲኖሩ ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡ የተጀመሩት ለውጦች ግን በኪራይ ሰብሳቢነትና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ቀጣይነታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ መስራት አንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በከሚሴ የቀበሌ አምስት ነዋሪና በጥብቅና ሙያ የሚተዳደሩት አቶ አብዱ መሐመድ በበኩላቸው "በአካባቢው የኦሮሚኛ ቋንቋ እውቅና አግኝቶና ሰርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት በትምህርት ቤቶች መሰጠቱ ህዝቡ በራሱ ጥረት ያቆየው ባህልና ማንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል አስችሎታል" ብለዋል፡፡ በተለይ ህዝቡ በራሱ ቋንቋ መዳኘቱ ተጠቃሚ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፍርድ ጉዳዮች በይግባኝ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሸጋገሩ ብቁና በቂ አስተርጓሚዎች ስለማይኖሩ ፈጣንና ቀልጣፋ ፍትህ ለመስጠት ተጽእኖ እየፈጠረ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በመጥፋት ላይ የነበረው የአርጎብኛ ቋንቋ እንዲያንሰራራ በአካባቢው የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ብሔረሰብ ወረዳ የመዲና ከተማ ነዋሪው ሼህ  ሰይድ ኢብራሂም ናቸው፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው "ለቋንቋው የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ተናጋሪዎቹ በመመናመን ቋንቋው የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበት ነበር " ብለዋል፡፡ መንግስት ለብሔር ብሔረሰቦች በሰጠው ልዩ ትኩረት በአንድ ቀበሌ ብቻ ተወስኖ የነበረው የተናጋሪው ቁጥር በወረዳው አምስት ቀበሌዎች መስፋፋት መቻሉን አስረድተዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር መደበኛ ባልሆነ መንገድ ትምህርቱ በተወሰኑ ትህርት ቤቶች እንዲሰጡ በማድረጉ ልጆቻቸውን ማስተማር መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ በወረዳው የቀበሌ ሰባት ነዋሪ አቶ አህመድ ኑሩ በበኩላቸው ወላጆቻቸው የአርጎብኛ ተናጋሪ ቢሆኑም በአካባቢው ቋንቋው እንዲስፋፋ ባለመደረጉ እሳቸውን ጨምሮ አብዛኛው ህዝብ የሚግባባው በአማርኛና በኦሮሚኛ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም ባህላቸውንና ታሪካቸውን መርምረው በጥልቀት እንዳያውቁ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ አርጎብኛ ተናጋሪ የኃይማኖት አባቶች በፈቃደኝነት ቋንቋውን በነጻ ስለሚያስተምሩ ልጃቸውን የማስተማር እድል እንዳጋጠማቸው ጠቁመዋል፡፡ ታዳጊ ወጣት ሲሃም ሰይድ በመዲና ከተማ በሚገኘው ሰንቀሌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ታዳጊዋ አርጎብኛን በትምህረት ቤቱ  እየተማረች እንደሆነ ጠቅሳ አሁን ለመግባባት በሚያስችላት ደረጃ ቋንቋውን እንዳወቀች ተናግራለች፡፡ የወረዳው መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ ኡመር በበኩላቸው በወረዳው በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች አርጎብኛን ከአንደኛ  እስከ አራተኛ ክፍል ለማስተማር የማስተማሪያና የመማሪያ መጻህፍት እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ትምህርቱ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡ ተማሪዎቹንም በብቃት ለማስተማር በከሚሴ መምህራን ኮሌጅ በተከፈተው የአርጎብኛ ትምህርት ክፍል 40 እጩ መምህራንን በመሰልጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ በመደበኛ ትምህርትም  ተግበራዊ እስኪሆን የወረዳው አስተዳደር በአምስት ቀበሌዎች  ባሉ አንደኛ ደረጃና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች  አርጎብኛ መደበኛ ባልሆነ መንገድ  ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን  አቶ ሰይድ ጠቁመዋል፡፡ ቋንቋው ከወረዳው ውጭ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ሾንኬና ጦልሃ መንደሮች አካባቢ በስፋት እንደሚነገር የገለጹት ደግሞ የወረዳው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አህመድ ኑሩ ናቸው፡፡ ቋንቋውን ለማበልጸግ የተጀመሩ ጥረቶች አበረታች ቢሆኑም  ለማሳደግ ከወረዳው ውጭ አርጎብኛ በሚነገርባቸው አካባቢዎች በመደበኛ ትምህርት  እንዲሰጥ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንዲሰጥ የሚፈልጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የአርጎብኛ ቋንቋን በስፋት ለማስተዋወቅም መዝገበ ቃላትና የመለማመጃ መጽሐፍ ታትመው ጥቅም ላይ መዋላቸውም ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም