ህዝብን ለማገልገል ትኩረት ያልሰጡ አመራሮችን በመለየት እርምጃ ይወሰዳል---የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር

131

ደብረ ማርቆስ መጋቢት 11/2011 ለውጡን ለማስቀጠል እና ህዝብን ለማገልገል ትኩረት ያልሰጡ አመራሮችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ   የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በልማት፣በዴሞክራሲ እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅት እንዳሉት ለውጡ ታላቅ ዋጋ ተከፍሎበት የተገኘና በማንኛውም መንገድ ሊቀለበስ የማይገባው ነው፡፡

በተፈጠረው ህዝባዊ መነሳሳት ልክ አመራሩ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ተገንዝቦ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለበት አመልክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የዞን አመራሮች መመሪያ አላሰራንም በሚል ጉዳዮችን በማወሳሰብ  ወደ ክልል ከመጠቆም  በህግ አግባብ በቅንነት መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

"ህብረተሰቡ ትክክለኛ ለውጥ ይፈልጋል" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ህዝቡን በተወሳሰቡ አሰራሮች እንዲማረር ማድረግ እንደማይገባ ተናግረዋል።

የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ እንዳይቀጥል በሚገፋፉ የህዝብ አገልጋይነት ባልተላበሱ፣ በዘረኝነት እና በሙሰኝነት የተተበተቡ አመራሮችን በመለየት  የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያና  የጎጃም ባህል ማዕከል ግንባታ አለመጀመር ፣ የመብራትና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ፣ ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ማነስ፣ ለኢንቨስትመንት ተብሎ አርሶ አደሮች የተፈናቀሉበት ቦታ ታጥሮ መቀመጥና በጸጥታ ችግር ምክንያት የሰዎች መገደል በውይይቱ ወቅት በተሳታፊዎች ከተነሱት ውስጥ ይገኙበታል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አንዳርጌ መላኩ  ወቅቱ የይቅርታና የመደመር ጊዜ ቢሆንም ሙሰኛና አምባገነን አመራሮች ለውጡ እንዳይቀጥል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጣቸው ፣የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሳይፈቱ ተባብሰው መቀጠላቸውን ጠቅሰዋል።

ወጣት ቢኒያም አካሉ በበኩሉ ከለውጡ በፊት ህዝብን ያማርሩ የነበሩ፣ የአቅም ችግር ያለባቸው፣ ሙስናና አድሏዊ አሰራር የሚታይባቸው አመራሮች አሁንም ድረስ በኃላፊነት እንዲቀጥሉ መደረጋቸው  በለውጡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጿል።

የህዝብ ችግር የማይሰማቸውና ለውጡን የማይፈልጉ አመራሮች እስካሉ ድረስ ለውጡ እውን ይሆናል ብሎ እንደማይጠብቅ ተናግሯል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳንኤል በላይ  ለውጡ ዳር እንዲደርስ ከቀበሌ ጀምሮ ቅሬታ የሚነሳባቸው አመራሮችን በመለየት ተጠያቂ የማድረግና የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

በእቅድ የተያዙ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የስራ እድል ፈጠራ ስራዎች የህዝቡን እርካታ በሚፈጥሩበት  አግባብ መከናወን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ለውጡ እንዲመጣ ባደረገው ጥረት ልክ  የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከአመራሩ ጎን ሆኖ ሊያግዝ  እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደሪ አቶ አብርሃም አለኽኝ  የደብረ ማርቆስ ባህል ማዕከልን ግንባታ ለማስጀመር ጨረታ ቢወጣም አለመሳካቱን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱን የመንግስት የልማት ድርጅቶች እንዲይዙት ተደርጎ በቅርብ ግንባታው እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

የአውሮፕላን ማረፊያው በተያዘው የበጀት ዓመት  ለሀገራዊ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ትኩረት በመሰጠቱ  ምክንያት በጀት ባለመያዙ በሚቀጥለው ዓመት ስራውን ለማስጀመር ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በውይይቱ ከደብረ ማርቆስ ከተማ የተወጣጡ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም