አካዳሚው የጀመረው የጥናትና ምርምር ስራዎች በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ለጥናት ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
አካዳሚው የጀመረው የጥናትና ምርምር ስራዎች በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ለጥናት ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓል ተባለ
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የጀመረው የጥናትና ምርምር ስራዎች በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ለጥናት ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓል ተባለ። ትልቁ የአካዳሚው ዓለማ ከሆነው ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት በተጨማሪ ችግር ፈቺ የስፖርት ጥናትና ምርምር ስራዎችን ያከናውናል። ባለፉት ሶስት ቀናትም አምስተኛው ሀገር ዓቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤ አካሄዷል። በዚህ ጉባኤ ላይ የተካፈሉ ባለሙያዎች እንደተናገሩት አካዳሚው ይህን መሰል ስራዎችን መጀመሩ በከፍተኛ ትምህርትና ተቋማት እንዲሁም በሌሎች ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎች ጥናት እንዲያደርጉ ተነሳሽነት ፈጥሮላቸዋል። በኮተቤ ዩኒቨርስቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ዶክተር አመንሲሳ ከበደ ይህን አይነት ስራ ሲጀመሩ አንዱ ዓለማቸው "ሰዎችን ለጥናትና ምርምር ስራዎች ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ነው" ይላሉ። አሁን ላይ የስፖርት ሳይንስና ሌሎች ተያየዥ ዘርፎች ላይ ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ በማድረጉ በኩል አካዳሚው የተሰካ ስራን ሰርቷልም ይላሉ። በጅማ ዩኒቨርስቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ዶክተር ወንድምአገኝ ደምሴ በበኩላቸው የአካዳሚው የጥናትና ምርምር ጉባኤ መጀመሩ ባለሙዎችንም ጥናት እንዲያደረጉና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የአካዳሚው ልምድ በመውሰድ የስፖርት ሳይንስ የጥናትና ምርምር ጉባኤ እንዲያዘጋጁ አስችሏቸዋል ይላሉ። በቀጣይ ግን እንደዚህ ዓይነት ጉባኤ ሲዘጋጅ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካለት በሙሉ ማሳተፍ ይገባል ብለዋል። እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የጥናት ስራዎች ብቻ በአማርኛ የሚቀርቡ ሲሆን፤ በቀጣይ ግን ሰው በቀላሉ አንብቦ እንዲረዳቸው ለማድረግ ጥናቶችን በሙሉ በአማርኛ እንዲቀርቡ ማድረግ የተሻለ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የጥናትና ምርምር ስራዎች ዳይሬከተር አቶ ዳንኤል አፈወርቅ እንደተናገሩት አካዳሚው የጀመረው የጥናት ስራዎች ባለሙያዎች በጥናት ላይ እንዲያተኩሩ በማድረጉ በኩል በጠንካራ ጎን የሚነሳ ነው ብለዋል። ነገር ግን አሁንም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን የጉባኤው ተሳታፊ በማድረግ በኩል ሰፊ ስራ እንደሚጠይቅ ነው የገለጹት። አካዳሚው ባለፉት አምስተኛው ሀገር ዓቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይ በራሱ ወጪና በባለሙያዎች ፍላጎት የሚሰሩ የስፖርት የምርምር ስራዎችን በየዓመቱ እንዲቀርቡ እያደረገ እስካሁን ወደ 120 የሚጠጉ የምርምር ስራዎች እንዲቀርቡ አስችሏል።