ምክር ቤቱ የኳረንቲን ጣቢያዎች ግንባታ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገቡ አሳሰበ

52

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2011 በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ የእንስሳት ዝውውር ለማስቀረት የኳረንቲን ጣቢያዎችን ግንባታ በፍጥነት በማጠናቀቅ ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የግብርና  አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ የግብርና ሚኒስቴር እያከናወናቸው ያሉትን የ18 ፕሮጀክቶች ግንባታ ገምግሟል።

በግምገማውም የእንስሳትን ጤንነትና ህጋዊ ዝውውር በማረጋገጥ የእንስሳት የወጪ ንግድን ያቀላጥፋል የተባለው ኳረንቲን ፕሮጀክት ተጠናቆ በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገባ አሳስቧል።

ግብርና ሚኒስቴር የህዝቡን ፍላጎት በሚመልስና በሚጠበቀው ልክ የፕሮጀክት ስራዎችን እየፈፀመ እንዳልሆነም ተገልጿል።

በተለይ በጅግጅጋ ፣ ሚሌ ፣ ሁመራ፣ አልመሃልና መተማ የሚገነቡ የእንስሳት ጤንነትና ህጋዊነት መመርመሪያ ጣቢያዎች ረጅም ጊዜ የወሰዱና በተደጋጋሚ ግምገማ የተደረገባቸው መሆኑም ተነስቷል።

በመሆኑም የእንስሳት ህገ ወጥ ዝውውርን ለማስቀረት የኳረንቲን ጣቢያዎቹን ግንባታ በማፋጠን ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል።

ፕሮጀክቶቹ በመንግስት በጀት ፣ በድጋፍና በብድር የሚሰሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የግንባታው መጓተት ኪሳራ የሚያስከትል መሆኑም ተጠቁሟል።

ሚኒስቴሩ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ላይ በሚፈለገው ልክ አቅሙን አሟጦ እየሰራ አለመሆኑንና ራሳቸውን ችለዋል ብሎ ከፕሮግራሙ የሚያወጣቸው ዜጎች በስርዓት ያልታዩና ራሳቸውን ያልቻሉ ናቸው በማለትም ቋሚ ኮሚቴው አስተያየት ሰጥቷል።

የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻልና ከሚሰሩ አራት ፕሮጀክቶች የድርቅ መቋቋምና ዘላቂ አርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ከፍተኛ ሃብት ቢያዝላቸውም ከአንዱ በስተቀር ያልተሳኩ መሆኑን ገልጿል።

በዚህ ዓመት በአገሪቱ ካለው አለመረጋጋት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም ቢኖርም ውጤትን ጥራትንና ጊዜን መሰረት ተደርገው ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ አለመሆናቸውን አንስቷል።

ሚኒስቴሩ በበኩሉ ፕሮጀክቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ከመደበኛው ስራ በተለየ መልኩ ራሱን ችሎ መገምገም መጀመሩን አብራርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም