የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን የማሊ አቻው ነገ ይገጥማል

318

አዲስ አበባ  መጋቢት 11/2011 የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታውን ነገ  ከማሊ አቻው ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ያካሂዳል።

ከቀኑ 10 ሰአት ላይ የሚካሄደው ጨዋታው በጃፓን ቶኪዮ እ.አ.አ በ2020 ለሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ የሚደረግ የማጣሪያ ጨዋታ ነው።

የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድኑ በህዳር ወር 2011 ዓ.ም ባደረገው የአፍሪካ ዞን የኦሎምፒክ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሶማሊያ አቻውን 4 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል።

በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድኑ ለጨዋታው ቅድመ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሲሸልስ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጎ 1 ለ 0 እና 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።

ተጋጣሚው የማሊ ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን በሁለት ተከፍሎ ዛሬ ማታና ነገ ጠዋት አዲስ አበባ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ናምቢያዊው ጃክሳን ፓቫዛ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

የነገው ጨዋታ የስታዲየም መግቢያ ዋጋ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የስታዲየም መግቢያ ዋጋ እንደሆነም ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ባማኮ ላይ ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የማሊ አቻውን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ  በቀጣዩ ዙር ማጣሪያ ከሩዋንዳ፣ ሞሮኮና ዴሞክራቲክ ኮንጎ አንዳቸውን የሚያገኝ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ይህን ዙር ካለፈች ደግሞ በታህሳስ 2012 ዓ.ም በግብፅ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ አገሮች የኦሎምፒክ ውድድር የመሳተፍ አድል ይደረሳታል።

በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ከወጣች ደግሞ ለቶኪዮ የእግር ኳስ ውድድር በቀጥታ አልፋ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሎምፒክ እግር ኳስ ውድድር ትሳተፋለች ማለት ነው።

ጃፓንን ጨምሮ 16 አገሮች በሚሳተፉበት የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከአፍሪካ አህጉር በወንዶች እግር ኳስ ሶስት አገሮች ይወከላሉ።

እ.አ.አ በ2020 በጃፓን ርዕሰ መዲና ቶኪዮ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታ የእግር ኳስ ዘርፍ በአህጉራት ተከፋፍለው በሚደረጉ ከ23 ዓመት በታች ውድድሮች በሚመዘገቡ ውጤቶች መሰረት አገሮች ለውድድሩ የሚያልፉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ወንዶች ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድሮች ለመሳተፍ በተለያዩ ጊዜያት የማጣሪያ ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን እ.አ.አ በ2004 በአቴንስ፣  እ.አ.አ በ2008 በቤጂንግ አሎምፒክ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርጎ ሳይሳካለት ቀርቷል። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1956 በአውስትሪሊያ ሜልቦርን ኦሎምፒክ የእግር ኳስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታ ማድረጓን መረጃዎች ያመለክታሉ።