በምስራቅ ጎጃም ዞን አራት ወረዳዎች የተከሰተውን ተምች መቆጣጠር ተቻለ

81
ደበረ ማርቆስ  ግንቦት 23/2010 በምስራቅ ጎጃም ዞን አምስት ወረዳዎች ከ190 ሄክታር በሚበልጥ የበቆሎ ማሳ ላይ የተከሰተውን የተምች ወረርሽኝ መቆጣጠር  መቻሉን የዞኑ  ግብርና መምሪያ ገለጸ። የመምሪያው የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ ቀኘ ገዜ  እንደገለጹት ባለፈው አመት በዞኑ ተከስቶ የነበረው የተምች ወረርሽኝ በዚህ አመትም በበቆሎ ሰብል ላይ ዳግም ተከስቷል። በማቻከል፣ በደብረኤሊያስ፣ በደብረማርቆስ ዙሪያና አነዳድ ወረዳዎች የተቀሰቀሰው የተምች ወረርሽኝ ወደሌሎች አካባቢዎች ሳይዛመት መቆጣጠር የተቻለው ኬሚካል በመርጨትና በባህላዊ መንገድ በእጅ ለቅሞ በማስወገድ ነው። ለርጭት ስራውም ከ164 ሊትር በላይ ፀረ-ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቅሰው ከ10ሺህ የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎችም በመከላከል ስራው ተሳትፈዋል፡፡ ተምቹ ወደሌሎች የሰብል አይነቶችም ሆነ በመኽር ሰብል እንዳይዛመት ከክልል እና ከዞን ከ600 ሊትር በላይ ተጨማሪ ኬሚካል ለወረዳዎች ቀርቦ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል። አርሶ አደሩም በልማት ቡድን አደረጃጀቱ በየጊዜው የማሳ ላይ አሰሳና ቅኝት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል። የደብረማርቆስ ዙሪያ ወረዳ የብራጌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር እውነቱ ተሻገር በመስኖ ባለሙት ሩብ ሄክታር የበቆሎ ሰብል ላይ የተከሰተውን ተምች ኬሚካል በመርጨት እንደተቆጣጠሩት ገልጸዋል። ተምቹ በማሳቸው ላይ ዳግም እንዳይከሰትም በየቀኑ ማሳቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በመስኖ እያለሙት ባለው ግማሽ ሄክታር የበቆሎ ሰብል ላይ የተከሰተውን ተምች ኬሚካል በመርጨትና በእጅ በመልቀም መከላከላቸውን የተናገሩት ደግሞ በደብረኤሊያስ ወረዳ የገነቴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር በላቸው ምህረት ናቸው። በመኽር ወቅት በአካባቢው በስፋት የሚመረተው የበቆሎ ሰብል በመሆኑም ተምቹ ወደሌሎች ማሳ እንዳይዛመት መንግስት በበቂ ሁኔታ ኬሚካል እንዲያቀርብላቸው ጠይዋል። በዞኑ ባልፈው የበጋ ወቅት በሁለተኛ ዙር መስኖ ከ15ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ሰብል እየለማ እንደሚገኝም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም