የስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰብ የሚያጋጥመውን የሃብት ሽሚያ ለማካካስ እየሰራሁ ነው-ግብርና ሚኒስቴር

235

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2011 በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ ያለው ስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰብ የሚያጋጥመውን የሃብት ሽሚያ ተጽዕኖ ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ በትግራይ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሱማሌ ክልል ባሉ 16 ወረዳዎች ባሉ 27 መጠለያ ጣቢያዎች ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞች ይኖራሉ።

በነዚህ አካባቢዎች ያሉ የስደተኛ ተቀባይ የሆኑ ማህበረሰቦች ስደተኞቹ በዛ አካባቢ በመስፈራቸው ሊቀንስባቸው የሚችለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት ለማካካስ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

በሚኒስቴሩ የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ንጋቱ ቦጋለ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤  በስደተኞች ተቀባይ ማህበረሰብ አካባቢ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የገቢ ማሳደጊያና የማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲዳረሱ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው።

በትምህርት ዘርፍ 54 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ተጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህም ሌላ የሰውና የእንስሳትን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ 16 የሰው እና 10 የእንስሳት ጤና ኬላዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

አካባቢዎቹን ለማስተሳሰርም ከ20 በላይ መጋቢ መንገዶች በዚህ ፕሮጀክት ከተሰሩ ስራዎች መካከል እንደሚገኙ ነው የጠቀሱት።

በአጠቃላይ በስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ልማት ፕሮጀክት 216 አነስተኛ ተቋማት ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን አስተባባሪው አስረድተዋል።

አነስተኛ መስኖ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የተፋሰስ ልማት፣ የተራቆተ መሬት እንዲያገግም ማስቻል እየተሰሩ ካሉ ስራዎች መካከል ይገኙበታል።

በተለይ ስደተኞች ወደነዚህ ስፍራዎች በሚመጡበት ጊዜ ለማገዶ ፍጆታ የተቆረጡ ደኖችን እንዲያገግሙ ከማድረግ በተጨማሪ ህብረተሰቡ በሶላር የሚሰሩ የማብሰያ ማሽኖች ለስደት ተቀባዩ ህብረተሰብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ባለፈው አመት 6 ሺህ 750 የማብሰያ ማሽን የተከፋፈለ መሆኑን ያስረዱት አቶ ንጋቱ በዚህ አመት ቁጥሩን ወደ 7 ሺህ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጉዳት ደርሶበት የነበረ መሬት በ63 ውሃ ማቀቢያ ተጠቅሞ 623 ሄክታር የተበላሸ መሬት ዳግም እንዲያገግም ሲደረግ በዚህ አመት ደግሞ 1 ሺህ 500 ሄክታር መሬት እንዲያገግም እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከዚህም ሌላ የሰብልና የእንስሳትን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ገቢ ለማሳደግም ከግብርናው ስራ በተጨማሪ በሌሎች ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ስልጠናና ብድር እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በቀበሌ ደረጃ ባለው የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማዕከል ተደርጎ የሚሰራ በመሆኑ እንደሌሎቹ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ችግር በስፋት እንደማይታይበትም አስረድተዋል።

”የነዚህ ፕሮጀክቶች ስራ ግንባታ ከአለም ባንክ በሚገኝ ብድር የሚሸፈን ሲሆን ህብረተሰቡም 5 በመቶ የገንዘብና 10 በመቶ ደግሞ የጉልበት ድጋፍ ያደርግባቸዋል ነው” ያሉት።

ከዚህም ሌላ የፕሮጀክቱን ግዢና ጨረታ የሚያወጡት የአካባቢው ተወካይ ኮሚቴዎች ሲሆኑ የባለሙያ ክፍያ ብቻ ነው በኮንትራክተሩ የሚፈጸመው።

በዚህ አመት ሚኒስቴሩ 227 ደጋፊ ፕሮጀክቶችን ለመስራት አቅዶ በ155 ቱ ላይ አጠቃላይ የጨረታ ሂደት አልቆ 89ኙ ወደ ግንባታ መግባታቸውን ገልጸዋል።