በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር መምህራን ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

84

ጎንደር መጋቢት 11/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር መምህራን ድርሻቸውን እንዲወጡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አሳሰበ፡፡

በዞኑ ላለፉት አራት ወራት በጸጥታ ችግር ከ3ሺህ በላይ መምህራን ከሥራ ገበታ የተስተጓጎሉ ሲሆን፣ ከ100 በላይ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ተዘግተዋል፡፡

ትምህርት ቤቶቹን በሚከፈቱበት ሁኔታ በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርት አመራሮች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በዚሁ ወቅት እንዳስገነዘቡት መምህራን የሰላም ጥረቱ አንድ አካል በመሆን የመማር ማስተማር ሂደት የሰመረ እንዲሆን በግንባር ቀደምነት ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ መቀስቀስ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ 

ለዚህም ከትምህርት አመራሩ ጋር  ሆነው ልዩ እቅድ በማዘጋጀት ፈጥነው ወደ ትግበራ መግባት እንዳለባቸው ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

የማጠናከሪያ ትምህርት ከመስጠት ጀምሮ በሣምንቱ መጨረሻ ቀናት የትምህርት ማካካሻ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጸዋል።

መምህራን በሚደረግላቸው ጥሪ መሠረት ፈጥነው ወደ ተመደቡባቸው ትምህርት ቤቶች በመሰማራት ሙያዊና ዜግነታዊ  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዶክተር ይልቃል ጠይቀዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ በበኩላቸው በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ከ100 በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ከ3ሺ በላይ መምህራንም ከሥራ ገበታ ተስተጓጉለው ቆይተዋል ብለዋል፡፡

በአካባቢው የሰፈነው ሰላም ለትምህርት አሰጣጥ  ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ከ11 በላይ ትምህርት ቤቶች በዚህ ሳምንት መግቢያ ተከፍተው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በቃጠሎ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰባት ተቋማት ውጪ ያሉትን ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሥራ የሚጀምሩበት ዕቅድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

መምህራን በተመደቡባቸው ትምህርት ቤቶች በመገኘት ከትምህርት አመራሩ፣ ከወላጆችና ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተው እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል፡፡

የላይ አርማጭሆ ወረዳ መምህራን ማህበር ተወካይ አቶ ብርሃኑ አወቀ በበኩላቸው ማህበሩ በዞኑ የተስተጓጎለውን ትምህርት ለማስቀጠል ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የታች አርማጭሆ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ተክለሃይማኖት እሸቴ  በበኩላቸው ከሥራ የተለዩትን 419 መምህራንን ወደ ሥራ ገበታ ከመመለስ ጀምሮ የማካካሻ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የመማር ማስተማር ሥራውን ለማሳካት እገዛ እንደሚያደርግ  አስታውቀዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በጭልጋ፣ በምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ፣ በታች አርማጭሆና በላይ አርማጭሆ ወረዳዎች 50ሺህ ያህል ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ተለይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም