የባላንጣ እቴጌዎች ዲፕሎማሲ

157

አየለ ያረጋል (ኢዜአ)

ኢትዮጵያ በጥንት ስርዓተ መንግስት ታሪኳ መራሂታት ነበሯት። ክብረ ነገሥት ባያበረታታትም ዙፋን በተባዕት ብቻ ተወስኖ አያውቅም፣ ለበርካታ ዘመናት ንግሥታትና ንግሥተ ነገስታትም ዙፋን ተቆናጠው አልፈዋል። ደራሲ ታደለ ገድሌ (ዶክተር) 'የንግስታት ገድሎችና የፍቅር ታሪኮች' በሚለው መፅሐፋቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥልጣን ጨብጠው ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ብልህና ጠንካራ እንስቶች እንደነበሩ ያወሳል። ለአብነትም ንግሥት ማክዳ (ከ1013 ዓ.ዓ)፣ ኒካንታ ህንደኬ (በ730 ዓ.ዓ)፣ ተካውላ ህንደኬ (333 ዓ.ዓ)፣ ኒኮውሲሰስ ህንደኬ (233 ዓ.ዓ)፣ አውሲና ንግሥት (በ88 ዓ.ዓ)፣ ደኮትሪስ ሕንደኬ ንግሥት ፮ኛ (በ24 ዓ.ዓ)፣ ንግስት ህንደኬ ፯ኛ(በ34 ዓ.ም)፣ ጌርሳሞት ንግሥት (በ42 ዓ.ም)፣ ዋከና ንግሥት(በ230 ዓ.ም)፣ አህየዋ ሶፊያ ንግስት (በ299 ዓ.ም)፣ አድሃና ንግሥት ፩ኛ (369 ዓ.ም)፣ አድሃና ንግሥት ፪ኛ (412 ዓ.ም)፣ ንግሥት ዮዲት ጉዲት (በ850 ዓ.ም)፣ ንግሥት ዘውዲቱ ምኒልክ (1909 ዓ.ም) ጠቅሰዋል። ነገሥታቱ በየነገሱበት ዘመን ታሪክ ሰርተው አልፈዋል።

በ'ኢምፓወር አፍሪካ' ድርጅት በየወሩ የሚያዘጋጀው መርሃ ግብር 'የኢትዮጵያ ሴቶች የፖለቲካ ትግል ትናንትና ዛሬ' በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በስቲያ (መጋቢት 09 ቀን 2011 ዓ.ም) ማምሻውን ተካሂዷል። በመንግሥታቱ ሴቶች ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሮ የልፍኝ አበጋዝ የሴት ካቢኔ መሾም እንደ ብርቅ በሚታይባት ኢትዮጵያ በጥንት ዘመን ግን ከ100 በላይ ሴቶች አገሪቱን መምራታቸውን ይገልጻሉ። እናም በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ትግል የዛሬ ሳይሆን ትናንትም የነበረ እንደሆነ ያብራራሉ። ከንግስተ ነገስታትነት በተጨማሪ ሴቶች በንጉሥና በንጉሠ ነገሥታት ባለቤትነት (እቴጌነት) ትልቅ አገራዊ የፖለቲካ ተዋናይ ሆነዋል። ለአብነትም እቴጌ መስቀል ክብራ (የአጼ ላልይበላ ባለቤት)፣ የቀኝ እመቤቷ ንግስት እሌኒ (የብዕደማርያም ሚስት)፣ እቴጌ ሠብለ ወንጌል (የአፄ ልብነድንግል ባለቤት)፣ ባቲ (እቴጌ) ድል ወንበራ (የግራኝ አህመድ ሚስት)፣ እቴጌ ምንትዋብ (የአጼ በካፋ ሚስት)፣ እቴጌ ጣይቱ (የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ባለቤት) ያነሳሉ። እቴጌ ጣይቱ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን እያማከሩ አገሪቱን አዘምነዋል፤ እቴጌ ሠብለ ወንጌልና እቴጌ ምንትዋብ በመከራም፣ በተድላም ጊዜ ከባላቸው፣ ከልጃቸውና ከልጅ ልጃቸው ጋር በቆራጥነት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን ተጋፍጠው አገር መርተዋል።

የሴቶች ፖለቲካ መሪነት በአገር ብቻ ሳይሆን በየወጡበት ማኅበረሰብ/ጎሳ መራሂያትም ሆነዋል። የሲዳማ ንግስት ፉራ፣ በወሎ ውስጥ የነበሩት እንደ ወርቂትና መስታወት የመሳሰሉ ወይዛዝርት ባለታሪኮችን በምሳሌነት ያወሳሉ። ከቅድመ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ምንጭ ግን በጋብቻና የነገሥታት ወይም የልዑላን ዘር መሆን ነበር ባይ ናቸው። ያም ሆኖ ግን ሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎና በአገር ጉዳይ ላይ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ወይዘሮ የልፍኝ ይናገራሉ። ከላይ የተጠቀሱት ነገስታትና እቴጌዎች ሁሉም አስደናቂ ታሪኮች አላቸው። ከነዚህ መካከል ግን የሁለት እቴጌዎችን የአንድ የመከራ ጊዜ ገድል ማንሳት ሴቶች በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸውን ብልሃትና ሚና ማሳያ ይሆናል። የእቴጌ ሠብለወንጌልና የባቲ(እቴጌ) ድል ወምበራን የዘመነ ጦርነት ዲፕሎማሲ።

እቴጌ ሠብለ ወንጌል በስመ መንግስታቸው 'ወናግ ሰገድ' የተባሉት የአጼ ልብነድንግል ብቸኛ የህግ ባለቤት ናቸው። (ሌሎች ነገሥታት ከሌሎች ጎሳዎች ከአንድ በላይ ሚስት ያገቡ ነበር፤ ልብነ ድንግል ግን በእቴጌ ሠብለወንጌል ተወስነዋል)። ሠብለወንጌል አራት ወንዶች (ፊቅጦር፣ ያዕቆብ፣ ገላውዲዮስና ሚናስ) እና አራት ሴቶች (ታዖድራ፣ ወለተቅዱሳን፣ ሰበነጊዮርጊስና ዓመተጊዮርጊስን) ወልደዋል። በደም ግባታቸው ተወዳዳሪ ያልነበራቸውና ሃይማኖተ ፅኑዕ የሚባሉት እቴጌ ሠብለወንጌል በ1518 ዓ.ም የነገሱትን አጼ ልብነድንግልን ካገቡ ጀምሮ እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው በቀጥታም በተዘዋዋሪም አገር መርተዋል። በሸዋ የረር ቤተ መንግስታቸው በድሎት ሲኖሩ በ1519 ዓ.ም የግራኝ ወረራ ወደ ሰሜን በስደት ተዋግተዋል። ልጃቸው አቤቶ ፊቅጦር በጦርነቱ ተገድሏል፤ ሌላው ልጃቸው ሚናስ (በኋላ አጼ) ተማርኳል። የኋላው ገላውዲዮስም በጦርነቱ አንገቱን ተቆርጧል። ባለቤታቸው (ልብደድንግል) ከቦታ ቦታ እየተሳደዱ በመጨረሻ ደብረ ዳሞ ላይ ሞቷል። ይህ ሁሉ ሲሆን እቴጌዋ መከራና ስደቱን ችለው ለአምስት ዓመታት ከሸዋ እስከ ኤርትራ ተንከራተዋል፤ በአሳሹ ቫስኮደጋማ ልጅ ክርስቶፎር ደጋማ የተመራውን የፖርቱጋል አጋዥ ጦር ከልጃቸው (ከገላውዲዮስ) ጋር አስተባብረው ድል ነስተዋል።

ከሠብለወንጌል እኩል የሚነሱትው ሴት የእቴጌዋ ባላንጣ ባቲ ድል ወንበራ ናቸው። 'እቴጌ' እንደሚባለው 'ባቲ' የሚል የማዕረግ ስም ያላቸው ድል ወንበራ በኤደን ባሕረ ሰላጤ (የአሁኗ ጅቡቲ) ገዥ የነበሩት የኢማም ማህፉዝ ልጅ መሆናቸው ይነገራል። የጦረኛው ኢማም አህመድ (አህመድ ግራኝ) ባለቤት ናቸው። በግራኝ አህመድ ዘመቻ በወታደሮቻቸው ተቃውሞ ሲገጥማቸው ወደ ጎን በመተው ከባለቤታቸው ጋር ዳገት፣ ቁልቁለቱን፣ ጋራ ሸንተረሩን ወጥተው ወርደዋል። በጦርነት ወቅትም ሁለት ልጆችን ወልደዋል። ከቆላማው የአዳል ግዛት ወደ ደገኛው ማዕከላዊ መንግስት ወረራ ሲደረግ ከባለቤታቸው ጋር ዘምተዋል። ለአምስት ዓመታት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ጦርነት ስፍር ቁጥር የሌለው ሰው ከሁለቱም ወገን አልቋል። በስተመጨረሻ ግራኝ በጎንደር ወይና ደጋ (አርባያ በለሳ) በጦርነቱ ሲገደል ባቲ ድል ወንበራ የተበታተነ ሠራዊቱን አስተባብረው በአዋጊነት ከፊት መሩ እንጂ ወደኋላ አላፈገፈጉም። (መጨረሻ ላይ ግን እንደ ስማቸው ድል ሳይቀናቸው ወደ ዘይላ አፈገፈጉ)። ልጃቸው መሃመድም ተማርኮባቸዋል። በኋላም የቀድሞ ባለቤታቸውን የእህት ልጅ የነበሩትን የሐረሩ ገዥ አሚር ኑር ኢብንን አግብተው ዓላማቸውን ለማሳካት ጥረዋል።

ድል ወንበራና ሠብለወንጌል ይመሳሰላሉ። ሁለቱም በጦርነቱ የተሳተፉ ጠንካራ ሴቶች ናቸው። ሠብለወንጌል የክርስቲያኑን ደጋማ ክፍል በመከላከል፣ ድል ወንበራ ደግሞ የሙስሊሙን ሰራዊት በመምራትና በማዋጋት ገድል ሰርተዋል። ሁሉቱም የትዳር አጋራቸውን አጥተዋል። ሁለቱም ልጆቻቸው (አቤቶ ሚናስና መሃመድ) ተማርከውባቸዋል። ስደትና መከራን ተጋፍጠዋል። በየግላቸው እምነትና ጉልበት በብርቱ የታገሉ ባላንጣዎች፣ የሴት ተምሳሌቶች ናቸው። ዋናው ግን ልጆቻቸው የተማረኩባቸው እናቶችና ጦር አዛዦችም ነበሩና ባላንጣ እቴጌዎች ልጆቻቸውን በዲፕሎማሲ በሰላም ተለዋውጠዋል። ነገሩም እንዲህ ነው።

የአጼ ልብነድንግል ልጅ አቤቶ ሚናስ (በኋላ አጼ) በጦርነቱ ወቅት ተማርከው ለአዳል ከፍተኛ ጠባቂነት በሚቆጠሩት የቱርኩ ሱልጣን ሱሌማን ስር እስረኛ ነበሩ። አህመድ ግራኝ ከሞተ በኋላ የተማረከው የድል ወንበራ ልጅ በሠብለወንጌል ጦር እስረኛ ነበሩ። ሁለቱ እቴጌዎች ግን ምርኮኞቻቸውን ከማስገደል ይልቅ መደራደር ጀመሩ። 'ልጄን ስጭኝ፤ ያንቺን ውሰጂ' ድርድር። በጥርጣሬ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱም እልባት ሳያገኝ ልጆቻቸውን ተለዋወጡ። ሚናስ ከቱርክ በምጽዋ አድርጎ እናቱ እቅፍ ስር ገባ። መሐመድም ከጎንደር ተነስቶ ሐረር ከምትገኘው እናቱ (ድን ወንበራ) እቅፍ ስር ገባ። ባላንጣ እቴጌዎችም በዲፕሎማሲያቸው ፍሬ ልጆቻቸውን አቅፈው ሳሙ። የሁለቱን ባላንጣ እቴጌዎች ዲፕሎማሲ አይነት ገድል የነበራቸው ሴቶች ይኖራሉ። የሴት አመራሮች (መራሂታት) ተምሳሌት የሚሆኑ እንስቶች።

ወደ የትናንት በስቲያው መድረክ ልመለስ። ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰና ሌሎች ታዋቂ ሴቶች በታደሙበት መድረክ ስለዛሬውና የወደፊቱ የሴቶች ፓለቲካዊ ተሳትፎ ተነስቷል። ሴቶች ድንቅ ዲፕሎማቶች ቢሆኑም እንደ ሴት ግን በጋራ ጉዳይ ተደራጅተው የሰሩበት ወቅት እንዳልነበር ተነስቷል። በ1935 ዓ.ም ከፖለቲካ ይልቅ በማህበራዊና መንፈሳዊ ተግባራት በሚታወቁት በእቴጌ መነን አስፋው መሪነት የተሰመረተው 'የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር' ቀዳሚው የሴቶች አደረጃጀት እንደሆነ ወይዘሮ የልፍኝ አንስተዋል። ነገር ግን ማህበሩ የጦር የልዑላን፣ መኳንንትና የጦር መኮንኖች ባለቤቶች እንጂ መላ ሴቶችን አሳታፊ እንዳልነበር ጠቅሰዋል። ያም ሆኖ በቤተሰብ ጤና፣ በሴቶችና ህጻናት ጤና፣ በወላጅ አልባ ህጻናት ጉዳዮችና መሰል ተግባራት ላይ ትልቅ ሚና መጫወቱን ያነሳሉ። ከመጀሪያዋ የፓርላማ አባል (የከንቲባ ገብሩ ደስታ ልጅ ስንዱ ገብሩ) ጀምሮ የሴቶች ትግል እያደገ መምጣቱን ያስታውሳሉ። በደርግ ዘመንም ከአምስት ሚሊዮን አባላት በላይ የነበረው የኢትዮጵያ አብዮታዊ ሴቶች ማኅበር በማህበራዊ መስኮች ትልቅ ሚና እንደነበር ያነሳሉ። በጸረ ደርግ ትግልም ከ4 ሺህ በላይ ሴቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል። ''ነገር ግን በደርግ ወገንም ሆነ በጸረ ደርግ ትግሉ የነበሩ ሴቶች የጋራ አጀንዳ ኖሯቸው ያደረጉት ትግል እምብዛም ነው'' ይላሉ። ከደርግ ውድቀት በኋላ ከጥቂቶች በስተቀር ሴት ታጋዮች ወደ ጓዳ እንጂ ወደ አደባባይ የፖለቲካ መሪነት አለመውጣታቸውንም ይጠቅሳሉ። በኢህዴግ ዘመን ከ1992ቱ ሶስተኛው አገራዊ ምርጫ ጀምሮ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ያስረዳሉ። የወቅቱን የዶክተር አብይ አህመድ የ50፡50 ካቢኔ ስብጥርን ደግሞ በመልካምነቱ ያወሳሉ።

የሴቶች ፖለቲካዊ ትግል ግን በቁጥር እንደማይወሰን የመድረኩ ተሳታፊ ሴቶቹ ያምናሉ። በኢትዮጵያ አባዊ ስርዓት (Patriarchy System) መንግስት የሴቶች አመራር ቁጥር ይልቅ በወንዶች በተቀረጸ አሰራር (set up) ለሚገቡት ሴቶች ውሳኔ ሰጭነት መስራት ይገባል፣ ተወካዮችን ማገዝ እንደሚገባ ነው ሲገለጽ የነበረው። ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ ሴቷ ወደ መሪነት መምጣት በራስ መተማመን (confidence) ብቻ ሳይሆን 'ራስን መሆን' (authentic) መቻል አለባት ትላለች። የሴቶችን እውነተኛ በየትኛውም ደረጃ ለሚገቡ ሹመኞችም የአመራርነት ስልጠና እንደሚያስፈልጋት ታምናለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሴራና ውሸት እንደሚያስፈልግ የምታምነው ሶሎሜ፣ ይህ ለሴቷም ለወንዱም ፈተና ለፖለቲካዊ ትግል አንዱ ተግዳሮት ነው። ሴቷ ወደ አደባባይ በምትወጣበት የዕድሜ ክልል 'ጋብቻና ውልደት' የራሱ አሉታዊ ተዕጽኖ እንዳለውም በመድረኩ ተነስቷል።

የሴቶች የሥልጣን ደረጃ በኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥታት ዛሬም ድረስ በሥርዓተ ጾታ እኩልነት የማያምኑ በርካቶች መሆናቸው የማይካድ ነው። የሴቶች እኩልነት ተቀባይነት እየቀነሰ በተለይም አስተዳደር ነክ ጉዳዮች ለወንዶች የተተወ መሆኑ እሙን ነው። ሴቶች ጥንት የነበራቸውን ዓይነተኛ ሚና ለማስጠበቅ በዘመናዊው እሳቤ ሴታዊ እኩልነት (feminism) ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ በትናንትናው መድረክ ሴቶቹ በአጽንኦት አንስተዋል። በወቅቱ የስልጣን ሹመቶች ከሴቶች አባላት ድጋፍ ይልቅ 'የኔ ብሄር አልተወከለም' የሚሉ ድምጾች እንደሚበዙ የምትገለጸው ሰሎሜ፣ ሴቶች ግን የአገሪቱ ግማሽ ቁጥር ያላቸው ስለሆኑ 'ትልቋ ብሔረሰብ ሴቷ ናት' ብለዋል። እናም የሴቶች የወደፊት ፓለቲካዊ ትግል እንዲሰምር በፖለቲካ ፓርቲዎች አባልነት ብቻ ሳይሆን በግል ተመራጭነት በመጭው አገራዊ ምርጫ ለህዝብ እንደራሴነት መወዳደር አለባቸው ተብሏል።

'ሴቶች የሚሰባሰቡበት፣ የጋራ አጀንዳ የሚያራምዱበት ንቅናቄ ያስፈልጋቸዋል' የሚለው ግን የመድረኩ ሃሳቦች ማሰሪያ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም