የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት ባለኃብቶች ከኢትዮጵያ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በሽርክና እንዲሰሩ ድጋፍ እየተደረገ ነው

622

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2011 የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬት ባለኃብት ከኢትዮጵያ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በሽርክና እንዲሰሩ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችና የንግድ ማኅበረሰብ የምክከር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር እንደገለፁት የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬት ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ እየተሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅትም ባለኃብቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸው ይህም መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግሥትም እነዚህ በላኃብቶች ከኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ ጋር በሽርክና እንዲሰሩ አቅጣጫ ማስቀመጡን አምባሳደሩ ገልጸዋል። 

ለዚህም አስፈላጊውን የኢንቨሰትመንት ካበቢ የማመቻቸትና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በጋራ ለመፍታት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ከዚህ ቀደም የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬት ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በግብርና ዘርፍ በስፋት በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራታቸውንም አስታውሰዋል።

ለዚህም የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ለኢትዮጵያ ያላቸው ቅርበት በኢትዮጵያ ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

እንደ አምባሳደር ደዋኖ ገለፃ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የምክክር መድረክም በአገራቱ መካከል የተደረሰውን የምጣኔ ኃብታዊ ግንኙነት እንዲሁም የንግዱን ማኅበረሰብ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው።

በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የኢኮኖሚክ ሚኒስትር የውጭ ንግድ ምክትል ተጠሪ አብዱላ አህመድም የአገራቸው ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጉት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ቀደም ሲልም በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለኃብቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥም ከዚህ በላይ መጨመር አለበት ነው ያሉት። 

በኢትዮጵያ ከ50 በላይ የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬት ባለኃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘረፎች ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ዓመታዊ የንግድ ልውውጥም ከ850 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል።

በምክክር መድረኩ ከኢትዮጵያና ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ከእያንዳንዳቸው ከ80 በላይ የንግድ ማኅበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በነገው ዕለትም አውደ ርዕይ በማሳየት የምክክር መድረኩ ይጠናቀቃል።