በትግራይ ክልል ባህላዊ መድኃኒትን ከዘመናዊው ጋር አጣጥሞ ለማምረት በቅንጅት እየተሰራ ነው

189

መቀሌ መጋቢት 11/2011 የትግራይ ክልል ባህላዊ መድኃኒትን ከዘመናዊው ጋር አጣጥሞ ለማምረት ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት እየሰራ  መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ 445 ባህላዊ መድኃኒት ቀማሚዎች ተደራጅተው በመሥራት ላይ ናቸው።

በቢሮው የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ባህረ ተካ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የሚዘጋጀውን ባህላዊ መድኃኒት ከዘመናዊው ጋር አዋህዶ ጥቅም ላይ ለማዋል ከዩኒቨርሲቲው ጋር  በመሥራት ላይ ናቸው።

ባህላዊ መድኃኒት ከእጽዋት፣ከማዕድንና ከእንስሳት ተዋፅኦ እየተቀመሙ አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ አመልክተው፣የመድኃኒነት መጠናቸው በምርምር ታውቆና ተቀምሞ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በባህላዊ የመድኃኒት ቀማሚዎች የሚቀርብ መድኃኒት መጠኑ ታውቆና መለያ ተደርጎለት አገልግሎት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የቀማሚዎችን አቅም  በስልጠና በመደገፍና የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት እንዲያገኙም ተቀናጅተው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ 445 የባህላዊ ህክምና አዋቂዎች በዚህ ዓመት ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡

የመቀሌ ባህላዊ መድሃኒት ባለሙያዎች ማህበር ሊቀመንበር መሪጌታ ፀሃየ የዕብዮ እንዳሉት በሙያው ያላቸውን ዕውቀት መሰባሰባቸው ባህላዊውን ሕክምና ወደ ዘመናዊ ደረጃ ለማሳደግ ያግዛቸዋል።

በሙያው የሚነግዱና ዕውቀት የሌላቸው ሕጋዊ ያልሆኑ ሰዎችን ለመለየት ያስችለናል ብለዋል፡፡

ማህበሩ ለባህላዊ መድኃኒት የሚያገለግሉ እጽዋትን ለማልማት የመሬት ጥያቄ  እንደሚያቀርብ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለባህላዊ መድኃኒት ግብዓት የሚሆኑ እጽዋት ልማት፣ አያያዝና አጠባበቅ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የማህበሩ አባል መሪጌታ መዓዛ  አደነ ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሜዲካል አንትሮፖሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር መምህር ምትኩ ገብረ ሕይወት በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባህላዊ ሕክምና ለዘመናዊ ሕክምና መነሻነቱን በመረዳት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ባህላዊ ሕክምና መረጃ በማሰባሰብና ምዝገባ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ባህላዊ መድኃኒት መጠናቸው ታውቆና ተቀምመው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ከባህላዊ ሐኪሞቹ ጋር መስራታቸውን  ተናግረዋል፡፡

ለመድኃኒትነት የሚውሉት እጽዋትና ማዕድንን በመረጃ አስደግፎ ለማስቀመጥ  የባህላዊ ሜዲካል አንትሮፖሎጂ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ምርምርና ጥናት እያደረጉ ናቸው ብለዋል።

ባህላዊ ሕክምናውን በሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናት ለባህላዊ ሐኪሞች ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን የተናገሩት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር መምህር ሀፍቶም ተክላይ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የባህል መድኃኒት ተጠቃሚ መሆኑን የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በዓለም ከሚመረቱት ዘመናዊ መድኃኒት ውስጥ 75 ከመቶ የሚሆኑት ምንጭ ተፈጥሮ ነው፡፡ በተለይ ለካንሰር ሕክምና የሚውሉ 50 ከመቶ ያህሉ መድኃኒት የእጽዋት ውጤቶች ናቸው፡፡

በባህላዊ መድኃኒት ከሚያዘወትሩ አገሮች መካከል ቻይና፣ ኮሪያ፣ ሕንድና ጀርመን ግንባር ቀደም ናቸው፡፡

በመልማት ላይ ከሚኖረው ሕዝብ 70 በመቶ የሚሆኑት የባህል መድኃኒት ይገለገላሉ።

በቻይና 90 በመቶ ሕዝብ  የባህል መድኃኒት ይጠቀማል፡፡ አገሪቱ የባህል መድኃኒት ወደ ውጭ በመላክ በዓመት እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም