ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ተወያዩ

94

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2011 በኳታር ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ከአገሪቱ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ጋር ተወያዩ።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኳታር ዶሃ የገቡት ዛሬ ማለዳ ነው። 

የመሪዎቹ ውይይት ያተኮረው በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም እና መሰረተ ልማት ዘርፎች ላይ ያላቸውን
ትብብር እና ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉበት መንገድ ላይ ነው።

ከዚህም ሌላ መሪዎቹ በአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይም መክረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኳታር ጉብኝት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።

ኢትዮጵያም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ የኳታር ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በአገሪቱ እንዲያፈሱ ፍላጎት አላት። ይህም እውን ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው።

የኳታሩ አሚር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2017 በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ነበር።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሻሻለ መምጣቱም ይነገራል።

ይህም የሆነው የአገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የልኡካን ቡድን አባላት በተለያዩ ጊዜያት ያደረጋቸውን ጉብኝቶችና የተፈራረሟቸውን በርካታ የትብብር ስምምነቶች ተከትሎ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም