በጅማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግርን ለመፍታት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

471

ጅማ  መጋቢት  10/2011 የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ መዋዠቅና  የተደራሸነት አገልግሎት  ችግር ለመፍታት ከህዝብ አስተዳደር አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

በኦሮሚያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የጅማ ዲስትሪክት ጽህፈት ቤት ከጅማ ከተማና ከጅማ ዞን አስተዳደር አካላት ጋር በአገልግሎት አሰጣጥና ተቀናጅቶ መስራት በሚቻልበት  ዙሪያ ዛሬ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ ወቅት የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ እንደገለጹት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስሪያ ቤት ከአስተዳደር አካላት ጋር መወያየት መጀመሩ አገልግሎቱ  ወደ ተሻለ ከፍታ ለማምጣት ያግዘዋል፡፡

መስሪያ ቤቱ ከዚህ  በፊት ከህዝብ አስተዳደር አካላት ጋር ተወያይቶ አለማወቁ በአገልግሎት አስጣጥም ሆነ ለተደራሽነት ስራው አጋዥ የሚሆኑ  የሃሳብ ግብአት እንዳሳጣው ተናግረዋል፡፡

በኤልክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ እንዳለም አንስተዋል፡፡

የሊሙ ገነት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ   አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ በበኩላቸው  የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት  ከውሃ፣ከኔትወርክ፣ከስልክና ከሌሎች አገልግሎት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱን በአግባቡ ካልሰጠ ደግሞ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው የጅማ ዲስትሪክት በአካባቢያቸው የሚሠጠው አገልግሎት ውስን በመሆኑ እንደተቸገሩ ጠቁመዋል፡፡

ከኃይል መቆራራጥና መዋዠቅ በላይም እስከ አንድ ወር ለሚደርስ ጊዜ አገልግሎት የሚያጡበት ሁኔታ እንዳለም አመልክተዋል፡፡

በቀጣይ ከህዝብ አስተዳዳር አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት መጀመሩ የሚያጋጥሙ ችግሮች   ስር ሳይሰዱ እንዲፈቱ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት  የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጫላ ቦንሳ  አሁን ባለው የዝቅተኛ የአገልግሎት አሰጣጥና የተደራሽነት ችግር ሁኔታ መቀጥል እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

” የአገልግሎት አስጣጥን በማዘመን ፋጣን ለማድረግ የማስፋፊያ ስራና የተጀመሩ ፕሮጆክቶችን ለመጨረስ ከህዝብ አስተዳደር አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት አስፈለጊ ይሆናል” ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጅማ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አክሊሉ  የጥራት ደረጃውን በጠበቀ አስተማማኝ የኃይል ስርጭትና ቀልጠፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

በቅርብ ማንኛውም ደንበኛ ጊዜንና ጉልበቱን ሳያባክን የፍጆታ ክፍያ ባለበት  ቦታ ሆኖ የሚክፍለበትን፣አገልግሎት ጥያቄን የሚያስመዘግብበትን እና ሌሎችም አሰራሮች እንደሚዘረጉ ገልጸዋል፡፡

ከአስተዳደር አካላት ጋር የወሰን ማስከበር፣የተጀመሩ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትን ለማጠናቀቅና አዲስ ለመጀመር  ከህዝብ አስተዳደር ጋር በቅንጅት መስራቱ እንደሚደግፉት የገለጹት ደግሞ በዲስትሪክቱ የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ክንፈ በላይ ናቸው፡፡ 

የኤሌክትሪክ ኃይል መስሪያ ቤት ቀድሞ ከነበረው ቀጠናዊ አደረጃጀት በፌዴራል የክልል አወቃቀር መሰረት መሆኑ ከህዝብ አስተዳደር ጋር በቅርበት ለመስራት አመቺነት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት በዘጠኝ ዲስትሪክት እና በ191 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የተደራጀ  መሆኑን በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡