መቶ በመቶ ትምባሆ የማይጨስባቸው ሆቴሎች ዕውቅና ተሰጣቸው

97
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 መቶ በመቶ ትምባሆ የማይጨስባቸው አራት ሆቴሎችና አንድ መንግስታዊ ተቋም ዕውቅና ተሰጣቸው። ዕውቅናው የተሰጠው በዓለም ለ31ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ26ኛ ጊዜ ‘ትምባሆና የልብ ህመም’  በሚል መሪ ህሳብ ትምባሆ የማይጨስበት ቀን  ዛሬ በተከበረበት ወቅት ነው። ዕውቅናው የተሰጣቸው አራራት፣ ሰሜን፣ ማግኖሊያና ተገን ሆቴሎችና የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ናቸው። ዕውቅናው የተሰጠው የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ጋር አንድ ላይ በመሆን ነው ተብሏል። የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አለምጸሀይ ጳውሎስ እንደተናገሩት ዕውቅናው የተሰጠው ድርጅቶቹን ለማበረታታትና ለሌሎች አርዓያ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው ብለዋል። በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የግምገማና ክትትል ባለሙያ አቶ ሚካኤል አብዩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ተቋማቱ በሆቴሎችና በመንግስታዊ ተቋማት  የትምባሆ ቁጥጥር ላይ ክትትል የማድረግና ስልጠና የመስጠት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በ2010ዓ.ም ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ኮከብ ባላቸው 18 ሆቴሎች ላይ  በተደረገ ቁጥጥርም አራት ሆቴሎች መቶ በመቶ ትምባሆ የማይጨስባቸው መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል። ባለፈው ዓመት 34 ሆቴሎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር መቶ በመቶ ትምባሆ የማይጨስበት  አንድ ሆቴል ብቻ  መገኘቱን የጠቀሱት አቶ ሚካኤል፤ ዘንድሮ መሻሻል መታየቱን እንደ አንድ ተስፋ ገልጸዋል። የሆቴሎቹ ኃላፊዎች በሰጡት አስተያያትም በሕብረተሰቡ ላይ ጉዳትን የሚያስከትሉ ተግባራትን መከላከል ግዴታ መሆኑንና ሌሎችም ይህንን ተሞክሮ ሊያስፋፉ እንደሚገባ አውስተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም