ኢትዮጵያ እኤአ በ2018 በጉዞ እና ቱሪዝም ዘርፍ 48 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ማስመዝገቧ ተገለጸ

94

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2011 የኢትዮጵያ የጉዞና ቱሪዝም የኢኮኖሚ ዘርፍ እኤአ በ2018 በ48 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን አለም አቀፉን የጉዞና ቱሪዝም ካውንስል ጠቅሶ ቱሪዝም ኒውስ ላይቭ  ድረ ገጽ አስነብቧል።

ተቋሙ ሪፖርቱን ያወጣው የዘርፉን የኢኮኖሚ ተጽእኖና ማህበራዊ አስፈላጊነት አስመልክቶ ባደረገው ዓመታዊ ምልከታ ነው።

የጉዞና ቱሪዝም ዘርፉ እኤአ በ2018 ለአገሪቱ ኢኮኖሚ 202 ቢሊዮን ብር ወይም 7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱ የተገለጸ ሲሆን ገቢው እአአ በ 2017 ከነበረው አፈጻጸም በ 59 ቢሊዮን ብር ወይም በ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ያለ ነው።

አሁን ላይ ዘርፉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ የ 9 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ ይዟል።

አለም አቀፉ ካውንስል ዘርፉን አስመልክቶ በ185 አገሮች ባደረገው ጥናት እአአ በ2018 በአለም አቀፍ ደረጃ  የዘርፉ ምጣኔ 3 ነጥብ 9 በመቶ ሲሆን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከዚህ እጅግ የላቀ ስኬት አስመዝግቧል።

አፍሪካ በዘርፉ ያስመዘገበችው ምጣኔ 5 ነጥብ 6 በመቶ ሲሆን ለ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል። ይህም በአጠቃላይ በአህጉሪቱ  ከተፈጠረው የስራ እድል 8 ነጥብ 3 በመቶ ድርሻ ይዟል።

ውጤቱ የተመዘገበው በቅንጡ ተጓዦች አማካኝነት ሲሆን በቱሪዝምና ጉዞ 79 በመቶ የሚጠጋውን ገንዘብ በማውጣት እነዚሁ ተጓዦች ቅድሚያ ሲይዙ፤ 21 በመቶ ድርሻውን የንግድ ተጓዦች ሸፍነዋል።

በተጨማሪ 77 በመቶ የሚሆነው የጉዞና ቱሪዝም ገቢ ከአለም አቀፍ ተጓዦች ሲገኝ 23 በመቶው ከአገር ውስጥ ተጓዦች ተገኝቷል።

“የኢትዮጵያ የቱሪዝምና የጉዞ እድገት በ2018  በአለም ላይ ከተመዘገቡት ስኬቶች ከፍተኛው ነው። በአለም አቀፍና በአህጉራዊ ደረጃ በዘርፉ ከተመዘገቡት ስኬቶች ጋር ሲነጻጸር ከየትኛውም አገር ሪከርድ በሆነ ደረጃ  ለውጥ አሳይቷል።'' ሲሉ የካውንስሉ ፕሬዝዳንት ግሎሪያ ጉቬራ  ተናግረዋል።

ስኬቱ በአገሪቱ የአቪየሽን ዘርፍ ጠንካራ አፈጻጸም በመታገዝና አዲስ አበባ የአፍሪካ አህጉር መዳረሻ በመሆን ባስመዘገበችው ከፍ ያለ እድገት የተገኘ እንደሆነም ገልጸዋል።

“አገሪቱ የጉዞና የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማሳደግ ያሳየችው ቁርጠኛ አካሄድ ኢኮኖሚውን በማሳደግ፤የስራ እድል በመፍጠር እና ማህበራዊ መስተጋብሩን በማሳደግ ለውጥ አስገኝቷል” በማለት ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም