''በክልሉ ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚደርስብን እንግልት የሚታደግ መፍትሄ እንሻለን''-ተገልጋዮችና አሽከርካሪዎች

61

አሶሳ መጋቢት 10/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚያደርስባቸው እንግልት የሚታደግ መፍትሄ እንደሚሹ  ተገልጋዮችና አሽከርካሪዎች ገለጹ፡፡

የአሶሳ ከተማ የመለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ''የታሪፍ ማሻሻያ ይደረግ'' በሚል ትናንት የግማሽ ቀን የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ወደ ሥራ ተመልሰዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በክልሉ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ሕዝቡን ያላረካና ከችግር ያላወጣ በመሆኑ ማስተካካከያ ሊደረግበት ይገባዋል።

የሸርቆሌ ከተማ ነዋሪው አቶ ሻምበል አጋዥ የትራንስፖርት ዘርፉ በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ላይ በሚታየው ያለ አግባብ ተጠቃሚነት ኅብረተሰቡ እየተጎዳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

መንግሥት ሕግ የሚጥሱ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች፣ ባለሃብቶችና አሽከርካሪዎች የሚያደርሱትን እንግልት እንዲያስቆም ጠይቀዋል፡፡

አቶ ወንድሙ ዳዊት የተባሉ አሽከርካሪ በበኩላቸው በክልሉ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ''ሙስና ተስፋፍቷል'' ይላሉ፡፡

ዓመታዊ ምርመራ ያልተደረገላቸው ብቃት የሌላቸው ተሸከርካሪዎች በማሰማራት ከሚደርሰው እንግልት ቀላል አለመሆኑን ተናግረዋል።ለአብነትም በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት የሚደርሰውን ጉዳት በማስረጃነት አቅርበዋል፡፡

መፍትሄው በየደረጃው በሚገኙ የዘርፉን ሥራ የሚመሩ ተቋማትን ''በአስቸኳይ ሪፎርም ማድረግ ነው'' ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

አቶ አለሙ ዋቅሹማ የተባሉ ባለሃብት በበኩላቸው በየጊዜው የነዳጅ የዋጋ ጭማሪ ቢደረግም፤ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ ተደርጎ እንደማያውቅ ያስረዳሉ፡፡

''ችግሩን ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ አሳውቀን ምላሽ አላገኘንም ''የሚሉት ባለሃብቱ፣ ''አሁንም ከአድማ ተመልሰን ወደ ሥራ የገባነው የሚመለከተው አካል አስቸኳይ መፍትሄ ይሰጠናል ብለን ነው''ብለዋል፡፡

የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ የሱፍ ያሲን ተጠይቀው ከትራንስፖርት ስምሪት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ለማስቀረት ከዚህ ወር መግቢያ ጀምሮ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከኅብረተሰቡ ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ሠራተኞች መኖራውን ቢሮው እንደደረሰበት ገልጸው፣ችግሩ ባለሃብቶችና በአሽከርካሪዎችም እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

ቢሮው በቅርቡ በጥናት የታክሲ ዋጋ ማስተካከያ ማድረጉን ያስታወሱት ምክትል ኃላፊው፣በመለስተኛ ተሸከርካሪዎች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እያለ ባለሃብቶች አድማ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

የባለሃብቶቹ  የታሪፍ ማሻሻያ ጥያቄ በመካከለኛ የሕዝብ  ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችና በባጃጅ ታክሲዎች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ቢሆንም ለጥያቄው በጥቂት ቀናት ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

በክልሉ ከ2 ሺህ የሚበልጡ መካከለኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችና ባጃጅ ታክሲዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም