ህብረቱ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚሰራ ብሔራዊ መድረክ ሊመሰርት ነው

58

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2011 የኢትዮጵያ ክፍላተ ሐገር ህብረት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚሰራ ብሔራዊ መድረክ ልመሰርት ነው አለ።

ህብረቱ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከሃያ አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ስብሰባ ከስምምነት የደረሱባቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ክፍላተ ሐገር ህብረት ዋና ጸሐፊ አቶ አገሬ አዲስ እንዳሉት ፓርቲዎቹ የጋራ እቅድ በማውጣት በኢትዮጵያዊነት ካስማ ላይ የቆመ ስርዓት በመመስረትና ከህብረቱ ጋር ለመስራት ተስማምተዋል።

ዋና ጸሃፊው በመግለጫቸው የሚመሰረተው መድረክ በተናጠል የሚደረገውን ትግል ለማቀናጀትና ለማስተሳሰር እንዲሁም የህግ የበላይነትና የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን ይሰራል።

የሰብዓዊና የዜግነት መብት እንዲከበር ከሚታገሉ ተመሳሳይ አቋም ካላቸው አገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት የተውጣጣ ብሔራዊ መድረክም ይመሰረታል።

በሚመሰረተው መድረክ የሰራተኛ ማህበራት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የወጣቶች ማህበርና ሌሎች የሲቪክ ማህበራትም የሚሳተፉ ይሆናል።

በዚህም እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ በመውረድ የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ መላው የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት በብሔራዊ መድረኩ ምስረታ ለመሳተፍ ከተካተቱ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም አንድነትን የሚያጠናክርና የጋራ ዓላማን በመንደፍ የ'ጎሳ ፖለቲካን' እንደሚታገሉ ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ክፍላተሐገር ህብረት ከሁለት ዓመት በፊት በአሜሪካ የተመሰረተ ሁለገብ የሲቪክ ማህበር ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማህበራትንና ሌሎች በኢትዮጵያዊነት ላይ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸውን ተቋማት በማስተባበር የሚሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም