የጅማ ከተማ ዓመታዊ የስፖርት ሻምፒዮና ተጀመረ

67

ጅማ  መጋቢት 10/2011 በመጪው ወር በነቀምት ከተማ በሚካሄደው የመላው ኦሮሚያ ልዩ ልዩ ስፖርት ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ያለመ ውድድር በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የከተማው ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጃይብ አባመጫ እንዳሉት በከተማው በሚገኙ 12 ቀበሌዎች መካከል ውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች እየተካሄደ ያለው በእግር ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በብስክሌት፣ በጠረጴዛ ቴኒስና በእጅ ኳስ የስፖርት አይነቶች ነው።

" የግል ሻምፒዮናም  የቦክስ፣ የክብደት ማንሳት፣ የቼዝና ዳርት ውድድሮችን ያካትታል" ብለዋል።

ለአሥስር ቀን በሚቆየው ውድድር 500 ስፖርተኞች አንደሚሳተፉ ታውቋል።

በውድድሩ ነቀምት ላይ በሚካሄደው የኦሮሚያ ሻምፒዮና ጅማ ከተማን ወክለው የሚሰለፉ ምርጥ ስፖርተኞች እንደሚለዩበት ተናግረዋል።

ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት፣ ታዳጊ ስፖርተኞችን ማበረታታትና የከተማውን ህዝብ የስፖርት ፍላጎት ማርካት ተጨማሪ የውድድሩ ዓላማዎች መሆናቸውንም አቶ አጃይብ አመልክተዋል።

ጽህፈት ቤቱ የከተማውን ስፖርት እንቅስቃሴ ለማጠናከር በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች 523 ታዳጊ ወጣቶችን በመመልመልና በፕሮጀክት በማቀፍ ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ትናንት ከሰዓት በጅማ ሁለገብ ስታዲዮም በተካሄደ የመከፈቻ ስነስርአት ላይ የጊንጆ  ቀበሌ እግር ኳስ ክለብ ከመንቲና ሂርማታ ባደረጉት ጨዋታ መንቲና ሂርማታ  2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡

በተያያዘ ዜና  ባለፈው ሳምንት አዲስ የተመሰረተው የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎች ማህበር ምርጫ አባላት ሳይሟሉ የተካሄደ በመሆኑ መሰረዙን የጅማው ስፖርት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም