ለቢራ ገብስ ግብይት የተሻለ ዋጋ ቢቀርብም በቂ ምርት ማግኘት አልተቻለም---ጎንደር ብቅል ፋብሪካ

104

ባህርዳር መጋቢት 10/2011 ለቢራ ገብስ ግብይት የተሻለ ዋጋ ብመድብም በቂ ምርት እያገኘሁ አይደለም ሲል የጎንደር ብቅል ፋብሪካ አስታወቀ።

የክልሉ ግብርና ቢሮና አርሶ አደሮች በበኩላቸው ፋብሪካው ከገበያው የተለየ ዋጋ እያቀረበ አለመሆኑን ገልፀዋል።

የፋብሪካው የቢራ ገብስ ምርት አቅርቦት መምሪያ ኃላፊ አቶ አደባባይ ፀጋው ለኢዜአ እንደገለፁት ፋብሪካው በዚህ ዓመት የአንድ ኩንታል ቢራ ገብስ ግዥ ዋጋን ከ1ሺህ 190 ብር ወደ 1ሺህ 540 ብር ከፍ አድርጓል።

በበጀት ዓመቱ ለግብአትነት ከሚያስፈልገው 240 ሺህ ኩንታል ገብስ ውስጥ 120 ሺህ ኩንታሉን በሀገር ውስጥ ከአልሚ አርሶ አደሮች ለመግዛት አቅዶ እንደነበር ተናግረዋል ።

"ይሁንና በማህበራት በኩል ሊቀርብለት የቻለው 42 ሺህ 400 ኩንታል ብቻ ነው" ብለዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ፋብሪካው  ከሀገር ውስጥ  ለመግዛት ያሰበውን ገብስ ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ባለመቻሉ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት አልተቻለም።

ካለፈው መኽርና አሁን በመስኖ እየለማ ካለው የቢራ ገብስ ተጨማሪ 20 ሺህ ኩንታል ምርት ለመግዛት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ፋብሪካው ባለፈው ዓመት ከአርሶ አደሩ ከ89 ሺህ 700 ኩንታል በላይ የቢራ ገብስ በመሰብሰቡ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳኑን አስታውሰዋል ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንየ አሰፋ በ2010/2011 ምርት ዘመን  በስምንት ዞኖች በዘር ከተሸፈነው 18 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ከ364 ሺህ ኩንታል በላይ የቢራ ገብስ  ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል ።

"የፋብሪካው የመግዣ ዋጋ ከገበያው የተሻለ ሆኖ ባለመገኘቱ አልሚው ምርቱን ገበያ አውጥቶ እንዲሸጥና ለምግብነት እንዲጠቀምበት አድርጎታል"ብለዋል።

ፋብሪካው ለአርሶ አደሩ በገበያው ካለው የተሻለ ዋጋ በመክፈል ምርቱን መሰብሰብ እንደሚኖርበትም አመላክተዋል ።

ፋብሪካው ምርቱን ለመረከብ አሻሻልኩት ያለው ዋጋ አሁን ካለው የገበያ ዋጋ የተለየ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን የላይ ጋይንት ወረዳ ነዋሪ  አርሶ አደር አለምነው ውቤ ናቸው።

የፋብሪካው የመግዣ ዋጋ ከገበያው የተሻለ ባይሆንም የቆየሁ ደንበኛ በመሆኔ ያገኘሁትን ምርት ለፋብሪካው ሸጪያለሁ" ያሉት አርሶ አደር  አለምነው በመኽር ያገኙትን 27 ነጥብ 5 ኩንታል ምርት ለፋብሪካው ኩንታሉን በ1ሺህ 540 ብር ሂሳብ መሸጣቸውን ተናገረዋል ።

በዞኑ እስቴ ወረዳ የዳት ጊዮርጊስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞገስ ሲሳይ በበኩላቸው በቢራ ገብስ ልማት መሳተፍ ከጀመሩ አራት ዓመት እንደሆናቸው አስታውሰዋል።

በመኽር ወቅት በቢራ ገብስ ካለሙት 1 ሄክታር ከሩብ መሬት ያገኙትን 25 ኩንታል ምርት በህብረት ሥራ ማህበራቸው በኩል ለፋብሪካው አቅርበው በመሸጥ 40 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል ።

"ፋብሪካው የሚረከብበትን ዋጋ ቢያሻሽልም ካለው የወቅቱ ገበያ ጋር ልዩነት የሌለው በመሆኑ በቀጣይ ማስተካከያ ካላደረገ ላለማስረከብ ወስኛለሁ" ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም