ሳተላይት ወደ ኅዋ ለማምጠቅ የሚደረገው የቅድመ ዝግጀት ሥራዎች ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል

65

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2011 ኢትዮጵያ በመጪው ዓመት ሳተላይት ወደ ኅዋ ለማምጠቅ እያደረገችው ያለው የቅድመ ዝግጀት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

የምክር ቤቱ የሰው ሃብትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ተቋም ላይ በዛሬው እለት የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በዚህ ጊዜ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እምዬ ቢተው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም ሳተላይት ወደ ኅዋ ለማምጠቅ በርካታ የቅድም ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።

ከቻይና መንግስት ጋር ተባብሮ መስራት፣ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች በስራው እንዲሳተፉና በቂ ልምድ እንዲያገኙ ማድረግና ዘርፉ ለአገሪቷ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲያመጣ የሰው ሃይል የማብቃት ስራ ከዝግጅት ስራዎች መካከል ይገኙበታል።

''የቅድመ ዝግጅት ስራው በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ በወቅቱ ሳተላይቱ እንዲመጥቅ የሚሰሩት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል'' ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የሚያደርጋቸውን የጥናትና ምርምር ተግባራት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በእንጦጦ ኦብዘርቫተሪና ምርምር ማዕከል አካባቢ የሚነሱ የወሰን ማስከበር ስራዎችን፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የግንዛቤና የቅንጅት ተግባራትን በትኩረት መስራት እንዳለበት አክለዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አገሪቷ ሳተላይት ወደ ኅዋ ለማምጠቅ የምታደርገው የቅድመ ዝግጅት ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው።

የመቆጣጠሪያ ጣቢያ የህንፃ ግንባታ፣ ዳታ መቀበያ ቁሳቁሶችን ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ የማስገባት፣ የሚሰሩትን ስራ የማረጋገጥ ተግባር፣ የሰው ሃይል የማሰልጠንና የማብቃተ ሥራ ከቅድመ ዝግጅቱ ስራዎች መካከል ይገኙበታል።

ለኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቅ ቅንጦት እንዳልሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን፣ ለስራ ፈጠራ፣ ለግብርና፣ ለጤና ለመሳሰሉት የአገልግሎት ዘርፎች መረጃ በመስጠት ውጤታማ ስራ ለመስራት እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

ዘርፉን በአገር ውስጥ በማስፋት ተፈላጊውን የሰው ሃብት ለማልማት ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገሮች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ የምርምርና ጥናት ስራዎችን ለህትመት የበቁ ሲሆን ተቋሙ ለኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ መሻሻልና ማደግ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

አፍሪካ ውስጥ እስካሁን ሳተላይት ያመጠቁ በጣት የሚቆጠሩ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ ስለመሆኗ ተናግረዋል።

ሳተላይቱን አገር ውስጥ ለመስራት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ለማምጠቅ የሚያስፈልገው ቴክኖሎጂና የሰው ሀይል ባለመኖሩ ወደ ሩቅ ምሥራቅ ያሰማራች ሲሆን ቻይና የገንዘብ፣ የሙያ እገዛና የማምጠቂያ ቦታ ለመስጠት ተስማምታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም