የመቀሌ ከተማ አስተዳደር መሬት ወስደው ባላለሙ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ ሊወስድ ነው

71

መቀሌ መጋቢት 9/2011 መሬት ወስደው ወደ ስራ ባልገቡ ባለሀብቶች  ላይ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን የመቀሌ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

መሬታቸው የተወሰደባቸው አርሶ አደሮች እስካሁን ለልማት ባለመዋሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

የአስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ  አቶ አማኑኤል ገብረእግዚአብሄር  ለኢዜአ እንዳሉት  የከተማ አስተዳደሩ ባካሄደው ጥናት ከዚህ ቀደም  መሬት ወስደው ወደ ልማት ያልገቡ ባለሀብቶች መኖራቸውን አረጋግጧል።

በአዲስ መልክ የተዋቀረው የከተማ አስተዳደሩ  መሬት ወስደው ወደ ልማት ባልገቡ  ባለሃብቶች ላይ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ልማት የገቡና ያልገቡ  ባለሀብቶች ከመለየት በተጨማሪ በተፈቀደላቸው የእፎይታ ጊዜ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የዘገዩና ተጨማሪ ማራዘሚያ ጊዜ የተሰጣቸው ባለሀብቶችን እንደሚያጣሩ ጠቁመዋል።

በሂደት ያሉ ግንባታዎች  የደረሱበት ደረጃ፣ በውላቸውና ባፀደቁት ፕላን መሰረት መቼ ማጠናቀቅ እንደነበረባቸው፣ አሁን ያሉበት ደረጃ የቁጥጥሩና የማጣራት ሂደቱ አካል እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

መረጃዎች ከተሰባሰቡና የማጣራት ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ለባለሀብቶች የተሰጠውን መሬት በመቀማት ወደ መሬት ባንክ የመመለስ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

የእርሻ መሬት የተወሰደባቸው አርሶ አደሮች መሬቱን አርሰው መጠቀም እየቻሉ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል ታጥሮ በመቀመጡ  ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢነት እንዳለው አቶ አማኑኤል አስታውቀዋል።

መሬታቸው ለልማት ከተወሰደባቸው አርሶ አደሮች መካከል  በዓይደር ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ግራኾላል ቦታ ነዋሪው አቶ መሓሪ ገራሰ  አንዱ ናቸው፡፡

መንግስት እርምጃ ባለመውሰዱ  ምክንያት ሳይለማ  መሬታቸው ከአስር ዓመታት በላይ  ታጠሮ መቀመጡ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡

በክፍለ ከተማው የዓዲሕሩስ መንደር ነዋሪ  አርሶ አደር ፅጋቡ ያለው በበኩላቸው  የተወሰደባቸው መሬት ያለምንም ልማት ታጥሮ በመቀጡ ማዘናቸውን ተናግረዋል።

መንግስት መሬት ወስደው ወደ ልማት ያልገቡት ባለሀብቶችን የመቆጣጠር ግዴታውን  ሊወጣ  አለመቻሉን አስረድተዋል።

የአካባቢውን ልማት ያነቃቃል ተብሎ ከሁለት ዓመታት በፊት በብረታብረት ስራ ተደራጅተው ለሚሰሩ ግለሰቦች የተሰጠው መሬት ምንም አይነት ልማት ያልተካሄደበት በመሆኑ መንግስት  እርምጃ መወስድ እንዳለበት ያመለከቱት ደግ ሌላው የአካባቢው አርሶ አደር ዮሐንስ ተካ ናቸው፡፡

የክልሉ መንግስት በቅርቡ 13 ሚሊዮን  ብር ላስመዘገቡ 222 ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬት ሰጥቷል።

መንግስት አልሚ ባለሀብቶች እንደሚያበረታታ ሁሉ መሬት ወስደው ወደ ልማት ባልገቡትም ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ እርምጃ እንደሚወሰድ መገለጹን  ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም