የጋምቤላ ክልል የአፈር ምርመራ ማዕከል ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አልቻልኩም አለ

576

ጋምቤላ መጋቢት 9/2011 የጋምቤላ ክልል የአፈር ምርመራ ማዕከል ከተቋቋመ ከ10 ዓመታት በላይ ቢሆነውም፤ተገቢውን አገልግሎት  መስጠት አልቻልኩም አለ፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ በበኩሉ ማዕከሉን የሚያጠናክር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ይላል፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ዴንግ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ማዕከሉ ባሉበት የግብዓት አቅርቦትና የባለሙያዎች እጥረት የሚፈለግበትን ያህል አገልግሎት በመስጠት ላይ አይደለም።

ማዕከሉ ካሉበት ችግሮች መካከል የላቦራቶሪ መሣሪያዎችና ኬሚካል እጥረት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

በማዕከሉ ባሉት ግብዓቶችና የሰው ኃይል ለመሥራትም የውሃ መሥመር አለመዘርጋት ችግር እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

ባለሙያዎቹ ያላቸው የትምህርት ዝግጅት ጋር ከማዕከሉ የሥራ መደብ ጋር እንደማይመጣጠንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ በክልሉ ያለውን የአፈር ዓይነትና ለምነት በመለየት የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድግ ቢሆንም፤ ትኩረት ስላልተሰጠው ውጤታማ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

በመሆኑም  ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ችግሮቹ  እንዲፈቱ  ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ላቦራቶሪውን ሥራውን የሚያስቀጥሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል፡፡

ከነዚህም ኬሚካልና ሌሎች የላቦራቶሪ ዕቃዎችን ለማሟላት ከተለያዩ ፕሮክቶችና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በተደረገላቸው ድጋፍ ግዢ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡

 የማዕከሉን ባለሙያዎችን ክህሎት ለማጎልበት አግባብ ካላቸው አካላት ጋር ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም  የባለሙያዎችን እጥረት ለማቃለል ቅጥር እንደሚፈጸም ገልጸዋል።

የውሃ አቅርቦት ችግር በቅርቡ እንደሚፈታ ዶክተር ሎው አስታውቀዋል፡፡

የጋምቤላ የአፈር ምርመራ ማዕከል ላብራቶሪ የግብርና ሚኒስቴር በአገሪቱ ካቋቋማቸው 17ቱ የአፈር ምርመራ ማዕከላት አንዱ ነው።