የላሊበላን ጥገና በበላይነት የሚመራ አብይ ኮሚቴ ሊቋቋም ነው

547

አዲስ አበባ  መጋቢት 9/2011 የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያን ጥገናን በበላይነት የሚመራ አብይ ኮሚቴ በቅርቡ እንደሚቋቋም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

አብይ ኮሚቴው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የላሊበላ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እና ከላሊበላ ቤተክርስቲያን ደብር የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ ነው።

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ እንዳሉት፤ በቅርቡ የሚቋቋመው አብይ ኮሚቴ አጠቃላይ የጥገና ሥራውን አቅጣጫ ይሰጣል።

አብይ ኮሚቴው የጥገና ስራው በተደራጀ መንገድ እንዲካሄድ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ አስተማማኝና ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚሰጥ አመልክተዋል። 

በላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያን የሚካሄደው የጥገና ስራ በኢትዮጵያዊያንና ፈረንሳዊያን ባለሙያዎች በጋራ የሚከናወን ሲሆን በቅርሱ ላይ የተጋረጠው አደጋ ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ እንደሚያገኝ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ኃይሉ ገለጻ ቅርሱን ለመጠገን ከፈረንሳይ መንግስት ጋር የተደረገው ስምምነት የገንዘብ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በጥልቅ ጥናት ላይ የተመሰረተ ጥገና እና እንክብካቤ ማድረግ ጭምር ነው።

ከዚህ በፊት በላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያን ላይ በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የተደረጉ ጥናትና ምርምሮች በሙሉ በአሁኑ ወቅት ጥገና ለሚያደርገው የቴክኒክ ቡድን ግብዓት እንደሚሆን አብራርተዋል።

በተለይ በጥናትና ምርምር ላይ የተሳተፉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን እና የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ማዕከል /ዩኔስኮ/ ባለሙያዎች በቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ መካተታቸውን አቶ ኃይሉ አመልክተዋል።

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፈው ሳምንት የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያንን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

የጉብኝታቸው ዓላማ ቅርሱ በአሁኑ ወቅት ያለበትን ጉዳትና ቅርሱን ከጥፋት ለመታደግ የፈረንሳይ መንግስት ሊያደርግ የሚገባውን ድጋፍ ለማጤን ነበር።

በፈረንሳይ መንግስት ወጪው የሚሸፈነው ፕሮጀክት ላሊበላን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ ቅርሶችን በአግባቡ ጠብቆ ለማቆየት ክብካቤ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።  

ከጥቂት ወራት በፊት የፈረንሳይ ቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ወደ ላሊበላ በመጓዝ ቅርሱ የሚገኝበትን ሁኔታ በተመለከተ ሦስት ጊዜ ጥናት ማካሄዳቸው ይታወሳል።     

በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ለማደስ የፈረንሳይ መንግስት የገንዘብ ድጋፍና የባለሙያ እገዛ ለማድረግ

ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የስምምነት ፊርማ ማድረጋቸው ይታወቃል።