ጋምቤላ የተማሪዎች ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ተጠናቀቀ

97

ጋምቤላ  መጋቢት 8/2011 በጋምቤላ ስታዲየም ለሁለት ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የመላው ጋምቤላ የተማሪዎች ዓመታዊ የስፖርት ውድድር ትናንት ምሽት ተጠናቀቀ።

ጋምቤላ ከተማ መስተዳድርን ጨምሮ በ14 ወረዳዎች መካከል ሲካሄድ በቆየው የስፖርት ውድድር የጋምቤላ ከተማ መስተዳድር በሁለቱም ጾታዎች በአትሌቲክስ አጠቃለይ አሸናፊ በመሆን ውድድሩን በአንደኝነት ፈጽሟል።

በዚሁ የውድድር ዓይነት ጎደሬ ወረዳ በሁለቱም ጾታዎች ሁለተኛ በመሆን ሲያጠናቅቅ፤ መኮይ ወረዳ በወንዶች፣ መንጌሽ ወረዳ ደግሞ በሴቶች ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በእግር ኳስ በተካሄደ ውድድር ጅካዎ እና አኮቦ ወረዳዎች ለፍጻሜ ቀረበው የመደበኛው የጨዋታ ጊዜ ያለ ግብ ተጠናቆ በመለያ ምት ጅካዎ ወረዳ አከቦ ወረዳን 3 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል።

በቅርጫት ኳስ ደግሞ ጋምቤላ ወረዳ አንደኛ፣ አኮቦ ወረዳ ሁለተኛ፣ አበቦ ወረዳ ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በቦሊ ቦል ኳስ ውድድር ኢታንግ፣ ጎግና አኮቦ ወረዳዎች በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ አግኝተዋል።

እንዲሁም በጠረጴዛ ቴንስ ጋምቤላ፣ ጎደሬና ጅካዎ ወረዳዎች በቅደም ተከትል ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ፈጽመዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ በውድድሩ ፍጻሜ ላይ እንደተናገሩት ስፖርት ለአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ እድገት ካለው ፋይዳ በተጨማሪ በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በኩል የላቀ ሚና አለው።

"መንግስት ይህንንበመገንዘብ የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ፣ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትና የወጣቱን ተጠቀሚነት ለማጠናከር የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቀርጾ በመስራት ላይ ይገኛል" ብለዋል።

በወረዳዎች መካከል የተካሄደው ውድድር በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ካለው ፋይዳ በተጨማሪ ውጤታማ ስፖርተኞችን ለመለየት ጭምር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጠይም በዘርፉ ለተጀመሩ ሥራዎች መጠናከር የክልሉ መንግስት የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ታይዶር ቻምባንግ በበኩላቸው እንዳሉት በወረዳዎች መካከል የተካሄደው ዓመታዊ የስፖርት ውድድር የዘርፉን እንቅስቃሴ ለማሳደግ ያግዛል።

ውድድሩ የተሻለ ውጤት ያላቸውን ስፖርተኞችን በመለየት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱ ውድድሮች ለማዘጋጀት ያለመ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ውድደሩ ለሦስተኛ ጊዜ በመቀሌ ከተማ ለሚካሄደው የመላው ኢትዮጵያ የተማሪዎች ውድድር ተሳታፊ ስፖርቶችን ለመለየት ያስቻለ መሆኑንም አቶ ታይደር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም