በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ተደረገ

105

ጎንደር  መጋቢት 8/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ፣ የአልባሳትና የቤት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

በጎንደር ከተማ ተገኝተው እርዳታውን ለክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን ያስረከቡት በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ተወካዮች ናቸው።

የክፍለ ከተማው የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ወይዘሪት አንቺነሽ ተስፋዬ እርዳታውን ባስረከቡብት ውቅት እንዳሉት ድጋፉ የመጀመሪያ ሳይሆን ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።

በዛሬው ዕለት ከተደረጉ ድጋፎች መካከል ከ900 በላይ ብርድ ልብስና አንሶላ፣ 35 የስፖንጅ ፍራሾች፣ 2ሺህ 847 የልብስ ሳሙና እንዲሁም  ከ100 ኩንታል በላይ የዳቦ ዱቄትና ሌሎችም የምግብ ፍጆታዎች ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም በክፍለ ከተማው በተለያዩ የአመራር ቦታዎች የሚሰሩ ሠራተኞችም ከወር ደመወዛቸው ያዋጡትን 67ሺህ 700 ብር የባንክ ቼክ አስረክበዋል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አማረ ክንዴ እርዳታውን ከተረከቡ በኋላ እንዳሉት የክልሉ መንግስት ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው በመመለስ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል ሥራ መስራት ጀምሯል፡፡

"በአዲስ አበባ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ለተፈናቃዮች ፈጥነው በመድረስ ፈር ቀዳጅ ናቸው" ያሉት ኃላፊው የክፍለ ከተማው ነዋሪዎችና አመራሮች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በክልሉ በአሁኑ ወቅት 90ሺህ 736 ተፈናቃዮች በ13 መጠለያዎችና ከዘመድ ጋር ተጠግተው ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም