ድጋፉ በትክክል እንዲደረሰን ክትትል ያስፈልጋል --የጌዲኦ ተፈናቃዮች

54

ዲላ መጋቢት 8/2011 ከመንግስትና ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የሚደረግልን ሰብአዊ እርዳታ በአግባቡ እንዲደርሰን ክትትል መደረግ አለበት ሲሉ ከአዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የጌዲኦ ተወላጆች ገለጹ።

የሰብዓዊ እርዳታዎችን በአግባቡ ለማድረስ እንቅፋት የሚሆኑ አሰራሮች ተገምግመው እርምጃ እንደሚወሰድም ተመልክቷል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ባወያዩት መድረክ ላይ በገደብ ወረዳ በመጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች እንደተናገሩት የእለት ደራሽ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች በአንዳንድ አካላት ተጽዕኖ ምክንያት በአግባቡ እየደረሳቸው አይደለም።

ከተፈናቃዮች መካከል ወይዘሮ ስንቄ ዳካ እንደተናገሩት ለወላድ እናቶች ማረፊያ እንዲሆን የተላከ ፍራሽና ሌሎች ቁሳቁሶች በአግባቡ ሊደርሳቸው አልቻለም።

ለዚህ ችግራቸው ምላሽ ለማግኘት ያደረጉት ጥረትም እንዳልተሳካ ተናግረው ወላድ እናቶች በቂ ድጋፍ እንዲደረግ የሚመለከታቸው አካላት ምልሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የቀረበውን እርዳታ እንኳን በአግባቡ ለተቸገሩ ወገኖች ማከፋፈል አለመቻል ተገቢ ባለመሆኑም እንቅፋት የሆኑ በየደረጃው ያሉ አካላት ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የሰላም ሚኒስትሯ መጥተው ባደሩት ጉብኝት ችግራቸውን ካዩ በኋላ ፍራሽና ሌሎች ድጋፎች የተላኩ ቢሆንም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሊዳረስ አለመቻሉን አስረድተዋል።

በማከፋፈል ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት ለእርዳታ የመጣውን ማንኛውንም ድጋፍ ሁሉንም እኩል በማየት ያለማዳላት ሊያዳርሱ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሌላው ተፈናቃይ አቶ ሱካሬ ከበደ በበኩላቸው ለተቸገሩት ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በአግባቡ እንዲደርስ እንቅፋት እየሆኑ ያሉ አካላት ሊጠየቁ እንደሚገባ ተናግረዋል።

መንግስትና ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ለተፈናቃዮች አገልግሎት እንዲውል የሚያቀርቡት ድጋፍ ለተለያየ ጥቅም እንዲውል ከማድረግ ይልቅ በትክክል ለተቸገሩት መድረሱን መከታተል እንደሚገባም አስረድተዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ እንደተናገሩት ለችግር ለተጋለጡ ተፈናቃዮች ከመንግስትና ከረዲኤት ድርጅቶች የሚቀርቡ ድጋፎች በተገቢው ፍጥነትና በፍትሃዊነት እንዲዳረስ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በከፋ ሁኔታ ጉዳት የሚገኙ ወላድ እናቶች፣ህጻናት እና ሌሎችም እየተለዩ አስቸኳይ የአልሚ ምግብ ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም በወቅቱ ሁሉም በልዩ ሁኔታ እርዳታ ይፈልግ ስለነበረ ለመቆጣጠር ማስቸገሩን ተናግረዋል። 

በተለያየ አጋጣሚ የድጋፍ አሰጣጡ ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ያሉ አካላት በየደረጃው ተለይተው አስፈላጊው የእርምት እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም አስረድተዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ሞልቶለት የነበረ ሰው በዚህ ሁኔታ ላይ ሲገኝ በርካታ ችግር ሊገጥመው የሚችል ቢሆንም በተቻለ መጠን መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት እየሰራ ነው።

ለተፈናቃዮች የሚደረግ እርዳታ መቋረጥ ስለመኖሩ የሚቀርቡ መረጃዎችም ከክልል ከዞንና ወረዳ የመጣው አመራር በአግብቡ እንዲያጠራው ተደርጎ የችግሩ ባለቤት በአስቸኳይ ተጠያቂ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግስት በዚህ በኩል እየተወሰደ ያለውን የማስተካከያ እርምጃ በቅርበት እንደሚከታተለው ሚኒስትሯ ለመድረኩ ተሳታፊዎች አስረድተዋል።

ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከምዕራብና ምስራቅ ጉጂ የተፈናቀሉትንና ያልተመለሱትንም ጨምሮ ከ208 ሺህ በላይ ሰው ድጋፍ እየቀረበለት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም