አፍሪካውያን ስደተኞች ለአህጉሩ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅኦ አላቸው - ተመድ

51
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 አፍሪካውያን ስደተኞች የአህጉሩን  ኢኮኖሚ እድገት ለመጨመር አስተዋፅኦ እንዳላቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ይፋ ያደረገው ሪፖርት አመለከተ። ተመድ አፍሪካውያን ስደተኞች እናት አገራቸውንም ሆነ በስደት ለሚኖሩበት አገር ኢኮኖሚ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዳላቸው የሚገልፅ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ስደት የሚታወቀው አሉታዊ በሆነ ጎኑ ቢሆንም በአፍሪካ ውስጥና ከአህጉሩ ውጭ የሚንቀሳቀሱ 41 ሚለዮን የተመዘገቡ የአፍሪካ ስደተኞች የአህጉሩን ኢኮኖሚ እየደገፉ መሆኑን ሪፖርቱ ያመላክታል። ሰርተው ከሚያገኙት ገቢ 85 በመቶውን ለአገራቸው እንደሚያፈሱ ተገልጿል። ከዚህም 19 ሚሊዮኑ ማለትም 53 በመቶ ያህሉ በአፍሪካ ውስጥ የሚደረግ ፍልሰት ሲሆን 17 ሚሊዮኑ ደግሞ አፍሪካን ለቀው ወደ ሌላው አለም የፈለሱ ናቸው። በተመድ የንግድና ልማት ኮንፈረንስ ዋና ፀሀፊ ዶክተር ሙኪሳ ኪቱይ ዛሬ ሪፖርቱን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ሲያብራሩ፤ 'የአፍሪካ ስደተኞች ለሄዱበት አገርም ሆነ ለትውልድ አገራቸው ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ' ብለዋል። ስደተኞቹ የራሳቸውን እውቀት ያሳድጋሉ፣ ከሚገኙበት አገር በሚልኩት ገንዘብ፣ ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጅ ሽግግርና ያገኙትን ልምድ በማካፈል የእናት አገራቸውን ኢኮኖሚ በመደገፍ የድህነት ምጣኔ ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋኦ እንዳላቸው ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሚሄዱበት አገር የስራ ቦታ ክፍተትን በመሙላት እንደሚያግዙ ገልፀዋል። ዳያስፖራዎች የአፍሪካን ባህልና ልዩ ምርቶች ለመላው አለም በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱም የገለጹት ዶክተር ሙኪሳ የኢትዮጵያ ጤፍ በአፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮፓ ተወዳጅ ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሆናቸውን ለአብነት በማንሳት አብራርተዋል። ኮትዲቭዋር፣ ጋና፣ ርዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ ከስደተኞች በሚመነጭ ገንዘብ ተጠቃሚ የሆኑ አገሮች መሆናቸውን በምሳሌነት ይጠቅሳል። ላይቤሪያ በስደት በውጭ ከሚገኙ ተወላጆቿ የምታገኘው ገንዘብ ከአገሪቱ ጠቅላላ ምርት 26 ነጥብ 7 በመቶውን ሲይዝ ሌሴቶም 18 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ በመሸፈን ከስደተኞች በሚገኝ ገንዘብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተገልጿል። የአፍሪከ አገሮች የሰዎችን ነፃ ዝወውርና የአፍሪካ ነፃ የአየር ትራንስፖርት ቀጠና መፈራረማቸው በአገሮቹ መካከል የዜጎችን ዝውውር በመጨመር ከዝውውሩ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያሳድገው ዋና ፀሀፊው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም