የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዐረብ አገሮች ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ዲንን አነጋገሩ

1333

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዐረብ አገሮች ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ዲንና በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ራሴሽ አልን ትናንት ማምሻውን በጽህፈት ቤታቸው  አነጋገሩ።

ዶክተር ወርቅነህና አምባሳደር አለን በፍልስጥዔም ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው መወያየታቸውን ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

በኢትዮጵያና በዐረብ አገሮች መካከል ያለው የትብብር ግንኙነት በሚጠናከርበት መንገድ ላይም መክረዋል።

በእስራኤልና ፍልስጥዔም መካከል ያለው ግጭት በድርድር እና በፖለቲካ ውይይት እንዲፈታ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ በዚሁ ጊዜ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያና የዐረብ አገሮች ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ግንኙነት አላቸው።

እ.አ.አ በ2009 የዐረብ ሊግ በኢትዮጵያ ኤምባሲ የከፈተ ሲሆን የሊጉ አባል አገሮችም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚፈልጉ በተለያዩ ጊዜያት በመግፅ ላይ ናቸው።

ሳዑዲ አረቢያ፣ ሱዳን፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶችና ግብጽ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ አገሪቷን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ እያደረጉ ከሚገኙ የአካባቢው አገሮች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።