ሕብረተሰቡ አሳዳጊ ለሌላቸው ሕጻናት ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

86
ነቀምቴ ግንቦት23/2010 አሳዳጊ የሌላቸው ሕጻናት ፍላጐታቸው ተሟልቶ በፍቅርና በእንክብካቤ ማደግ እንዲችሉ ሕብረተሰቡ ከጎናቸው በመቆም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ። 28ኛው የአፍሪካ ሕጻናት ቀን ትናንት በነቀምቴ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የነቀምቴ ከተማ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ደብሬ ፈቃዴ እንደገለጹት ሕጻናት ተገቢ ፍቅርና እንክብካቤ አግኝተው ማደግ አለባቸው። በመሆኑም መደገፍና ከጎናቸው መቆም የሕብረተሰቡ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ነው የገለጹት። ኢትዮጵያ ካለፋት ሁለት አስርት ዓመታት በላይ የሕፃናት መብቶች ኮንቬሽንና ሌሎች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን ተቀብላ ከማጽደቅ ባለፈ ለሕጻናት ደህንነት እየተጋች መሆኑንም ወይዘሮ ደብሬ አስረድተዋል። በዚህ በኩል ጽህፈት ቤቱ በነቀምቴ ከተማ ለችግር የተጋለጡ ሕጻናት ድጋፍና እንክብካቤ አግኘተው የሚያድጉበት ሁኔታ ለማመቻቸት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። "ለእዚህም እስካሁን ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ለችግር የተጋለጡ 350 ሕጻናት በቋሚነት የምግብና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል" ብለዋል። የአፍሪካ ሕጻናት ቀን መከበርም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል። በከተማዋ ባለፉት ሦስት ወራት በከተማዋ ሜዳ ላይ ተጥለው የተገኙ ዘጠኝ ሕፃናት በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲያድጉ ለአሳዳጊ እናቶች መሰጠቱንም አስረድተዋል። በበዓሉ ላይ የተገኙት ሕጻናቱን በጉዲፈቻ ለማሳደግ የወሰዱ እናቶችም ለሕጻናቱ ተገቢ እንክብካቤ በመስጠት ለማሳደግ  በሕዝብ ፊት ቃል ገብተዋል። ከበዓሉ ተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ቸርነት ዋቅወያ በሰጡት አስተያየት "ልጆቹ የፈጣሪ ስጦታና የሀገር አለኝታ መሆናቸውን ተረድተን ባለንበት አካባቢ መደገፍና መንከባከብ ይኖርብናል" ብለዋል። ለጉዲፈቻ የወሰዱትን ሕጻን እንደራሳቸው ልጅ አድርገው ተንከባክበው እንደሚያሳድጉ የገለጹት ደግሞ በከተማው የቀበሌ 03 ነዋሪ ወይዘሮ ሹከሬ ደረጀ ናቸው። ያላቸውን ሃብትና ንብረት ከወለዱት ልጅ ጋር እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን በሕግ ፍት በመቅረብ ሕጉ በሚያዘው መሰረት እንደሚፈጽሙም ገልጸዋል። ሌላዋ የጉዲፈቻ አሳዳጊ ወይዘሮ ዘርትሁን ነገራ በበኩሏቸው "ለማሳደግ የወሰድኩትም ልጅ እንደ አብራኬ ክፋይ በመቁጠር ከማንኛውም አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች በመጠበቅ ለቁም ነገር አበቃዋለሁ" ብለዋል። በበዓሉ ላይ የሕጻናት መብትና ግዴታን አስመልክቶ የከተማው ፍትህ ጽህፈት ቤት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥቷል። በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሕፃናትም የተለያዩ የመማሪያ መጻህፍትና መዝገበ ቃላት በሽልማት መልክ ተበርክቶላቸዋል። በዓሉ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት ገቢ ለማሰባሰብ የተለያዩ ጫረታዎች የተካሄደ ሲሆን በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ምስል የሚያሳይ ፎቶ ቀርቦ በ12 ሺህ ብር ተገዝቷል። የአፍሪካ ሕጻናት ቀን በደቡብ አፍሪካ ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘት ይገባናል፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋችን እንማር የሚል ጥያቄ በማንሳታቸው በግፍ የተጨፈጨፉትን ህጻናት ለማሰብ  በየዓመቱ የሚከበር ነው። በነቀምቴ ከተማ ሁለገብ አዳራሽ በተከበረው በዓል ላይ በርካታ ህጻናት፣ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም