በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ለተፈናቃዮች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

71

ጎንደር መጋቢት 7/2011  በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመጠለያዎች ሆነው ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች ሩብ ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ፡፡

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ቢያዝን ድጋፉን ለዞኑ ትምህርት መምሪያ ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ድጋፉ ተማሪዎች በቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት ከትምህርት ገበታ እንዳይለዩ ለማድረግ ነው፡፡

ለተፈናቃዮች  ከተሰጡት የትምህርት ቁሳቁስ መካከል 28ሺ 363 የመማሪያ ደብተሮች ከ13ሺ በላይ እርሳሶችና እስክርቢቶዎች ይገኙበታል፡፡

ድጋፉ ተፈናቃዮቹ በትምህርት ቁሳቁስ እጦት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ቢሮው ከማዕከላዊ ጎንደር በተጨማሪም በሰሜን ወሎ ቆቦና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ተወካይ አቶ ናትናኤል ቢምረው በበኩላቸው የትምህርት ቁሳቁስ በአይምባና በትክል ድንጋይ ጊዜያዊ መጠለያዎች ሆነው ለሚማሩ ከ1ሺ 600 በላይ ተማሪዎች ይሰራጫል፡፡

በዞኑ በግጭት ሳቢያ 113 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን የጠቆሙት ተወካዩ፣50ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም ሀይንኒከን ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በጭልጋና በአይምባ ጊዜያዊ መጠለያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ግምቱ 300ሺ ብር የሆነ 154 ኩንታል የዳቦ ዱቄት ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም